የተቆጡት ቻይናዊ አከራይ የተከራያቸውን ገመና አጋለጡ

ቻይናዊቷ ሊሳ ሊ በ1.1 ሚሊዮን የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮቿ ዘንድ እጅግ ትከበራለች። ሕይወቷ ያማረ፣ የተዋበ፣ ቅንጡ እንደሆነ የሚያሳዩ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያ በመልቀቅ ዝናን አትርፋለች።

ከሰሞኑ ግን ሊሳ ሊ ከአድናቂዎቿ የስድብ ውርጅብኝ እየደረሰባት ነው።

ለካስ ሊሳ በማኅበራዊ ሚዲያ እንደምትናገረው ሕይወቷ ውብ፣ ቤቷም ጥንቅቅ ያለ አልነበረም። ይህንን ያስተዋሉ የሊሳ አከራይ፤ የሊሳን እውነተኛ አኗኗር የሚያሳዩ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያ አሰራጭተዋል።

በእነዚህ ምስሎች የሊሳ ቤት ዝብርቅርቅ ብሎ፣ በቆሻሻ ተሞልቶ ይታያል።

ሊሳ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ቻይናውያን አንዷ ነበረች። ስለጎበኘቻቻው ድንቅ ቦታዎች፣ እራት ስለበላችባቸው ውድ ሆቴሎች ወዘተ በመጻፍ ትታወቃለች።

የሊሳ አከራይ ለማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ይፋ ያደረጉት ምስል ግን የሊሳ ሕይወት ከምትለው የራቀ መሆኑን ይመሰክራሉ።

የሊሳ አከራይ ቼን፤ ሊሳ ያልከፈለችው ውዝፍ እዳ እንዳለባት ይናገራሉ። ሊሳ ቤታቸውን በአግባቡ ባለመያዟ ክስ እንደሚመሰርቱባትም ዝተዋል።

የሊሳ አከራይ፤ "ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የምትመለከቷት ውብ ሴት የውሸት ናት፤ እጅግ አስቀያሚ ሕይወት ነው የምትመራው" ሲሉ ተናግረዋል።

የሊሳ እና የቼን ጉዳይ ቻይናውያን የሚጠቀሙበት ማኅበራዊ ሚዲያ 'ዊ ቡ' ላይ "መነጋገሪያ ሆኗል።

የሊሳን እውነተኛ ሕይወት የሚያሳዩ ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ከተሰራጩ በኋላ፤ አድናቂዎቿ ተቆጥተዋል። ለቀናት ሊሳን ሲዘልፏትም ነበር።

ሊሳ በበኩሏ፤ ባደረኩት ነገር ተጸጽቻለሁ ብላ ከአከራይ ይቅርታ ጠይቃለች።

"ላደረግኩት ነገር ኃላፊነቱን እወስዳለሁ" ያለችው ሊሳ፤ አከራይ ቼን ይቅር እንዲሏት ስትማጸን የሚያሳይ ቪድዮም ተሰራጭቷል።

ሊሳ "ዛሬውኑ ቤቴን አጸዳለሁ" ስትልም ቃል ገብታለች።

በ 'ዊ ቡ' ወደ 60,000 ሰዎች በሊሳ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ድርጊቷ ያስቆጣቸው ጥቂት ተከታዮቿ "ዋሾ" ብለዋታል። ከዚህ በኋላ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አንከተላትም ብለው 'አንፎሎ' ያደረጓትም አሉ።