በየትኛው አቀማመጥ ቢፀዳዱ ጤናማ ይሆናሉ?

ከሙሉ ሕይወታችን በአማካይ ወደ ስድስት ወር ያህሉን የምናሳልፈው ስንፀዳዳ መሆኑን ያውቃሉ?

በዓመት ውስጥ የአንድ ሰው ሰገራ ሲመዘን 145 ኪሎ ግራም ይሆናል። ይህ ማለት ደግሞ አንድ ሰው በዓመት ሁለቴ ከክብደቱ እጥፍ የሚመዝን ሰገራ ያስወግዳል ማለት ነው።

በሕይወታችን ግዙፍ ቦታ ያለው የመፀዳዳት ጉዳይ ከጤናችን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። ለመፀዳዳት የምትቀመጡበት መንገድ በጤናችሁ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የምታውቁ ስንቶቻችሁ ናችሁ?

ለመሆኑ መፀዳጃ ላይ ስንት ሰዓት ያጠፋሉ?

በ20ኛው ክፍለ ዘመን እኩሌታ ላይ በአፍሪካ ገጠራማ አካባቢዎች የሚሠሩ ሀኪሞች፤ አንዳችም ከ 'ጋስትሮኢንተስታይናል' (ምግብ የመፍጨትና ሰገራ የማስወገድ ሂደት) ጋር የተያያዘ የጤና እክል ያለበት ሰው አልገጠማቸውም ነበር።

ነገሩ ሀኪሞቹን አስገርሟቸው ነበር። ከአፍሪካ ውጪ በሌሎች ታዳጊ በሚባሉ አህጉሮችም ምግብ ፈጭቶ ሰገራ ከማስወገድ ጋር የተያያዘ እክል ያለበት ሰው እምብዛም አልነበረም።

መላ ምታቸው የነበረው ነገሩ የአመጋገብ ሥርዐት ውጤት ይሆናል የሚል ነበር። እውነታው ግን ያ አልነበረም። ሀኪሞቹ ለጥያቄያቸው መልስ ያገኙት፤ ከሰዎች ሰውነት የሚወገደው ሰገራ የሚጠራቀምበት የጊዜ ርዝመትና ሰዎች ሲፀዳዱ የሚቀመጡበት መንገድ ነበር።

ምዕራባውያኑ መፀዳጃ ቤት በገቡ ቁጥር ቢያንሰ ከ114 እስከ 130 ሰከንድ ይቆያሉ። በተቃራኒው ታዳጊ በሚባሉ አገሮች አንድ ሰው መፀዳጃ ቤት የሚቆየው ለ51 ሰከንድ ብቻ ነው።

ምዕራባውያኑ ቁጭ ተብሎ መፀዳዳት የሚቻልበት መጸዳጃ ሲጠቀሙ፤ ታዳጊ የሚባሉ አገሮች ደግሞ ቁጢጥ ብሎ መፀዳዳት ያዘወትራሉ።

ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ ለአጭር ጊዜ መፀዳጃ ቤት መቀመጥ ጤናማ ነው።

ስንፀዳዳ መቀመጫችን አካባቢ 90 ዲግሪ ይታጠፋል። ይህም በአካባቢው የሚገኘው ጡንቻ አንጀታችንን እንዲጫነው ያደርጋል።

ቁጭ ብሎ ለመፀዳዳት የሚያስችለው ፈጠራ

የመጀመሪያው መፀዳጃ ሥራ ላይ የዋለው ከጥንታዊ ሜሶፖታሚያ ሥልጣኔ ወዲህ እንደሆነ ይነገራል።

ከክርስቶስ ልደት 315 ዓመታት በፊት ሮም 144 የሕዝብ መፀዳጃ ነበራት። ሮም ውስጥ የተገነባውና 2,000 ዓመታት ያስቆጠረው መፀዳጃ፤ ጎን ለጎን የተሠሩ 50 የመፀዳጃ ጉድጓዶች የያዘ ነበር።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 1592 ላይ ውሃ የሚያፈስ መፀዳጃ ተፈልስፎ ነበር። 1880 ላይ ደግሞ አንድ እንግሊዛዊ ዓለምን ያስገረመ መፀዳጃ ይዞ ብቅ አለ።

መፀዳጃው ሰዎች ቁጭ ብለው የሚጠቀሙበት ሲሆን፤ ከመፀዳጃ ውስጥ ቆሻሻን ያስወግዳል።

የሚፀዳዱበት መንገድ ጤናዎ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?

ብዙዎች ለመፀዳዳት ሲያምጡ ይስተዋላል። ለዚህ ችግር ምክንያት ከሆኑት መካከል የምግብ አለመፈጨት፣ የሰገራ መድረቅና የአንጀት ህመም ይጠቀሳሉ። ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ ልንፀዳዳ ስንል የምንቀመጥበት መንገድም የጤና እክል ያስከትላል።

ምዕራባውያን የሚያዘወትሩት የመፀዳጃ አይነት ለጤና እክሉ ምክንያት እንደሆነ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ።

በኮርኔል ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ፕሮፌሰር አሌክሳንደር ኪራ፤ ሰዎች ቁጢጥ ከማለት ይልቅ ቁጭ ብለው እንዲፀዳዱ የተሠራው መፀዳጃ የችግሩ ምንጭ እንደሆነ ይናገራሉ።

ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ በምንፀዳዳበት ወቅት ጉልበታችንን ከ90 ወደ 30 ዲግሪ ከፍ በማድረግ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል።

እግራችንን ከፍ ስናደርግ አንጀታችንን ከመተጣጠፍ እናድናለን።

መፀዳጃ ፊት ለፊት ዱካ አስቀምጦ፣ በምንፀዳዳበት ወቅት እግራችንን ዱካው ላይ ማውጣትን ተመራማሪዎች ይመክራሉ።