በደቡብ አፍሪካው ዝርፊያ ከአርባ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ደቡብ አፍሪካውያን ሥራችንን ወስደበውናል ያሏቸውን ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ዜጎች ላይ ጥቃት አድረሰዋል። አመፀኞቹ የውጭ ሃገር ዜጎች ሱቆችንና ንብረቶችን በመዝረፍ እና በማቃጠል ላይ እንዳሉ ከሥፍራው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህንን ተከትሎም ከአርባ በላይ ደቡብ አፍሪካውያን ትናንት ማምሻውን ጀምሮ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ፖሊስ አመጸኞቹን ለመቆጣጠር አስለቃሽ ጭስ የተጠቀመ ሲሆን ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ መሆን ሲጀምሩ ደግሞ የጎማ ጥይቶችንም ጭምር ተጠቅሞ ነበር ተብሏል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጂፒ በተሰኘው የደቡብ አፍሪቃ ግዛት የሬስቶራንት ባለቤት የሆነው አቶ ተከስተ ሹምዬ ስለሁኔታው ጠይቀነው ነበር።

''የሌላ ሃገር ዜጎች የሆኑ አፍሪካውያን ላይ ነው ጥቃቱ የተሰነዘረው። በተለይ ደግሞ የመኪና ሽያጭ ላይ የተሰማሩ ናይጄሪያውያን ላይ ከእሁድ ጀምሮ ጥቃት ተፈጽሟል። እስካሁን በሰማሁት ዜና ከ50 በላይ መኪና ተቃጥሏል''በማለት ሁኔታውን ያስረዳል።

እሁድ ጠዋት ላይ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን እና አንድ ህንጻ እንደተቃጠለ ሁኔታው እስካሁን እንዳልተረጋጋ ተከስተ ይናገራል።

ተከስተ እንደሚለው በግምት ከአስር ቀናት በፊት ፕሪቶሪያ በተባለችው ከተማ የሃገሬው ታክሲ ሾፌሮች ከናይጄሪያውያን ሾፌሮች ጋር ተጋጭተው በናይጄሪያውያን በተተኮሰ ጥይት አንድ ደቡብ አፍሪካዊ መሞቱን ተከትሎ ትልቅ ብጥብጥ ተነስቶ ነበር።

በዚህም ምክንያት ላለፉት ቀናት ናይጄሪያውያንን ጨምሮ ከሌላ ሃገራት የመጡ ዜጎችን ንብረት መዝረፍና ማቃጠል ተበራክቶ እንደነበር ተከስተ ይናገራል።

''ይህ ዝርፊያና አመጽ ወደ ጆሃንስበርግ ተዛምቶ መጥቷል። እሁድ ዕለት ዝርፊያና ማቃጠሉ ተጀመረ። ቀደም ብሎ ግን ከሌላ ሃገራት የመጡ ዜጎችን እናስወጣለን የሚል ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ ደርሶን ነበር''።

ብዙ ኢትዮጵያውያን በሚገኙበት ጂፒ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በኢትዮጵያን ላይ የደረሰ ጉዳት አለ ወይ? ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ ተከስተ ሲመልስ፤ '' ጂፒ አካባቢ እስካሁን ምንም የደረሰ ነገር የለም። ግን ፕሪቶሪያ ውስጥ ሱቆች ሲቃጠሉ የአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ሱቆችም አብረው ወድመዋል። ግን እዚህ ጆሃንስበርግ የፖሊስ ቁጥሩ ከፍ ስላለ ብዙ ደፍረው አልመጡም'' ብሏል።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው ደቡብ አፍሪካውያን ወጣቶች ከሌላ ሃገራት የመጡ ዜጎች ስራችንን ቀምተውናል በሚል መነሻ እራሳቸውን በማደራጀት ሱቆች ላይ የመዝመት ሁኔታ ታይቷል ይላሉ።

''ከዚህ ጋር በተያያዘ ዜጎቻችን በስነልቦናም ይሁን ከዝርፊያው ጋር በተገናኘ የሚያጋጥማቸው ችግር አለ፤ ይህንንም ለመፍታት ከሃገሪቱ የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የሚቻለውን ሁሉ እየተደረገ ነው''።

አክለውም ''በእኛ ማህበረሰብ በኩል በቂ የሆነ ከለላ በማድረግ ላይ እና የዜጎች ንብረት እንዳይዘረፍ በመከላከል በኩል የተሟላ አይደለም በሚል ቅሬታ አለ'' ብለዋል።

ብዙ ናይጄሪያውን እና የናይጄሪያውያን ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ የናይጄሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆፍሪ ኦንዬማ ''ማሰብ የተሳናቸው ወንጀለኞች'' የፈጸሙት ተግባር ነው በማለት መሰል ተግባራት በአስቸኳይ እንዲቆም አሳስበዋል።

የውጭ ሃገር ዜጎች ንብረት የሆኑ ሱቆች መዘረፍና ማቃጠል የደቡብ አፍሪካ የዕለት ተዕለት አጋጣሚ እየሆነ መጥቷል። በቅርቡም መፍትሄ የሚያገኝ አይመስልም።

ብዙዎችም እንዴት ደቡብ አፍሪካውያን የሌላ አፍሪካ ሃገር ዜጎች ላይ ጥቃት ያደርሳሉ? ብለው ቢጠይቁም ጉዳዩ በቀላሉ ምላሽ የሚያገኝ ነገር አይደለም።

ምናልባት ስራ አጥ የሆነው የደቡብ አፍሪካ 28 በመቶ የሚሆነው ወጣት ስራ ቢያገኝ ይሄ ሁሉ ነገር በአንዴ ይቆም ነበር የሚሉም አልጠፉም።