ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መንታ ጠብቃ አምስት የተገላገለችው ኡጋንዳዊት እናት
መንታ ለመውለድ የጠበቀችው እናት ሶስት ሴቶችና ሁለት ወንዶች በድምሩ አምስት ልጆችን በመገላገሏ ድንጤ ላይ እንደወደቀች የሃገሪቷ ሚዲያ ደይሊ ሞኒተር ዘግቧል።
በሃገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ነዋሪ የሆነችው ሶፊያት ሙቴሲ ከዚህ ቀደም መንታ እንዲሁም ሶስት ልጆችን በአንዴ ተገላግላ የነበረ ሲሆን አንድ ልጅም እንዳጣች ጋዜጣው ዘግቧል።
"አምስት ልጆች መገላገሌ በጣም ነው ያስገረመኝ፤ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ለምርመራ የጤና ማእከል ሄጄ በታዬሁበት ወቅት የህክምና ባለሙያዎች መንታ እንዳረገዝኩ ነው የነገሩኝ" በማለት አግራሞቷን ለጋዜጣው አጋርታለች
የሚረዳትም አካል ባለመኖሩ ልጆቿንም እንዲያሳድጉላትም እርዳታን እየሻተች ነው።
እንደ ሞኒተር ዘገባ ከሆነ የመጀመሪያ ባሏን በሞት ያጣች ሲሆን የአሁኑ አጋሯ ደግሞ ሃያ ልጆች አሉት ተብሏል።
በኢጋንጋ ናካቩሌ ሆስፒታል አዋላጅ የሆነችው ሞውሪን ባቢን በበኩሏ አራሷም ሆነ ጨቅላዎቹ በሙሉ ጤንነት ላይ እንዳሉ ገልፃለች።
"በሆስፒታል በሰራሁባቸው አመታት አምስት ልጅ የወለደች እናት አጋጥሞኝ አያውቅም፤ አብዛኛውን ጊዜ መንታ ወይም ሶስት ልጆች ናቸው የሚያጋጥሙን፤ ህፃናቱ በሙሉ ጤና ቢወለዱም እንክብካቤንና ክትትልን ይሻሉ" ብላለች።