ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታዳጊዎቹ በገጣጠሟት አውሮፕላን ከደቡብ አፍሪካ ተነስተው ካይሮ ገቡ
ደቡብ አፍሪካውያን ታዳጊዎች ራሳቸው በገጣጠሟት ስሊንግ 4 አውሮፕላን ከኬፕታወን ደቡብ አፍሪካ ተነስተው ስድስት ቀን ያህል ከበረሩ በኋላ ካይሮ ግብጽ ገብተዋል።
አራት ሰዎችን የመሸከም አቅም ያላትን ይህች አውሮፕላን 20 ከተለያየ ዘርና ቀለም የመጡ ተማሪዎች ናቸው የገጣጠሟት።
የአብራሪ ቡድን አባላቱ በእስካሁን በረራቸው ከ12ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሸፈኑ ሲሆን ናሚቢያ፣ ማላዊ፣ ኢትዮጵያ፣ ዛንዚባር፣ታንዛኒያ እና ኡጋንዳን ረግጠዋል።
የ17 ዓመቷ ፓይለት ሜጋን ዌርነር የዩ ድሪም ግሎባል ፕሮጀክት መስራች ስትሆን በእስካሁን ስኬታቸው መደነቋን ትናግራለች።
"በቆምንበት ሀገር ሁሉ ልዩነት በመፍጠራችን ክብር ይሰማኛል።"
አክላም "የዚህ ፕሮጀክት ዓላማ አፍሪካውያን ምንም ነገር ለመስራት አእምሯችንን ካዘጋጀነው እንደምንችል ለማሳየት ነው" ብላለች።
እነዚህ ታዳጊዎች ከሚያበሯት አውሮፕላን ጎን ለጎን ሌላ ስሊንግ 4 አውሮፕላን በባለሙያ አብራሪዎች የበረረ ሲሆን በመንገዳቸው ላይ የተለያዩ የማነቃቂያ ንግግሮችን እያደረጉ ድካምና መሰላቸት እንዳይሰማቸው ሲያደርጉ ነበር።
ተማሪዎቹ አውሮፕላኑን የገነቡት ደቡብ አፍሪካ በሚገኝ አውሮፕላን ማምረቻ ከተሰራ ቁሳቁስ ሲሆን ለመገጣጠምም ሶስት ሳምንት ፈጅቶባቸዋል።
ግንባታው በሺዎች የሚቆጠሩ ጥቃቅን የአውሮፕላን ክፍሎች መገጣጠም ያካትት ነበር።
የሜገን አባት ዴስ ዌርነር፣ የንግድ አውሮጵላን አብራሪ ሲሆኑ ይህንን አውሮፕላን አንድ ሰው ሊገጣጥም ቢፈልግ 3000 ሰዓት ይፈጅበታል ሲሉ ተናግረዋል።
ሜጋን የዚህ ጉዞ አስገራሚ ነገሮች ተግዳሮቶቹ ናቸው ትላለች።
ኢትዮጵያ በሄዱበት ወቅት አዲስ አበባ ነዳጅ ማግኘት አልቻሉም ነበር።
"እዚያ ስንደርስ አብሮን የሚበረው ድጋፍ ሰጪ አውሮፕላን ነዳጅ ማፍሰስ ጀመረ። ስለዚህ እኔና ድሪያን ቫን ዴን ሂቨር ብቻ ጉዞውን ቀጠልን ብላለች" ሜጋን።
በሱዳን ሰማይ ላይም ስንበር በሀገሪቱ ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት የተነሳ ስጋት ገብቶን ነበር ስትል ትናገራለች።
ሜጋን የማብረር ፈቃድ ካገኙት ስድስት የቡድኑ አባላት መካከል አንዷ ስትሆን ስድስቱም እየተፈራረቁ ክንፎቿን በአፍሪካ ካርታ ያስጌጠችውን አውሮፕላን አብርረዋል።
አብራሪዎቹ ፍቃድ ሲሰጣቸው ከመሬት የሚኖራቸውን ርቀት የሚወስን የነበረ ሲሆን ከፍ ብሎ በደመና ውስጥ መብረር አልተፈቀደላቸውም ነበር።
የመጨረሻው የፓይለቶቹ በረራ ከአዲስ አበባ ግብፅ በአስዋን በኩል የነበረ ሲሆን ይህም አብራሪዎቹን የፈተነ እንደነበር ተጠቅሷል።
"ያለ ድጋፍ ሰጪ አውሮፕላን፣ ሁለት አዳጊዎች፣ እኔና ድሪያን ቫን ዴን ሂቨር ለአስር ሰዓታት ያህል በረናል" ብላለች ሜጋን።
ሁለቱ አብራሪዎች ግብፅ የአየር ክልል ውስጥ ከገቡ በኋላ ስለመንገዳቸው የአየር ንብረት መረጃውን የሚሰጣቸው ስርዓት ችግር አጋጥሞት ነበር። ስለዚህም በካይሮ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እንደ እቅዳቸው ከማረፍ በካይሮ ቅርብ ርቀት የሚገኝ የአየር ማረፊያ ማረፍ የተሻለ መሆኑን በመወሰን እዚያ አርፈዋል።
ይህ ትንሽ መረባበሽ ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን የተፈጠረውን ነገር ተቆጣጥረው በሰላም ማረፍ ችለዋል።
አውሮፕላናቸው ካረፈች በኋላ የተፈጠረውን ሲመረምሩ በአግባቡ ያልተያያዘ መስመር በመኖሩ ችግሩ መፈጠሩን ተረድተዋል።
ካይሮ እንደደረሱ የግብፅ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ሊያውሏቸው የሞከሩ ሲሆን ፓስፖርታቸውንና አብራሪ ፈቃዳቸውን ተነጥቀው ከአራት ሰዓት በኋላ የተፈጠረው አለመግባባት ተፈትቶ ነዳጅ ሞልተው በአስዋን በኩል ወደካይሮ በመብረር የካይሮ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አርፈዋል።