የእንስሳት ቀንድ ሽያጭን የሚደግፉት የቦትስዋናው መሪ ከዝሆን እግር የተሠራ ዱካ ስጦታ ሰጡ

የናሚቢያ፣ የዛምቢያና የዚምባብዌ መሪዎች አጥቢ እንስሳትን ላይ ያተኮረ ውይይት ለመካፈል ወደ ቦትስዋና አቅንተው ነበር። የቦትስዋና ፕሬዘዳንት ሞክወትሲ ማሲሲ ለሦስቱ ሀገራት መሪዎች ከዝሆን እግር የተሠራ ዱካ መስጠታቸውም ተሰምቷል።

ሦስቱ ሀገሮች እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ በእንስሳት ጥርስና ቀንድ ሽያጭ ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ እየጠየቁ ነው።

ከእንሳሳት ጥርስና ቀንድ ሽያጭ በሚገኘው ገንዘብ የእንስሳትን ደህንነት መጠበቅ እንችላለን የሚል መከራረርያ ያቀርባሉ።

ዝሆኖች በመላው አፍሪካ ከፍተኛ አዳጋ ከተጋረጠባቸው እንስሳት መካከል ይጠቀሳሉ። በዓመት 30,000 ዝሆኖች እንደሚገደሉ ይታመናል። በአህጉሪቷ ውስጥ በሕይወት የቀሩት 450,000 ገደማ ዝሆኖች እንደሆኑም ይነገራል።

ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች ሕገ ወጥ አደንን ለማስቆም ከዘየዷቸው መላዎች አንዱ የእንስሳት ጥርስና ቀንድ ሽያጭን ማገድ ነው። ሆኖም በርካታ ቁጥር ያላቸውና የሰው ልጆችን መኖሪያ ጥሰው የሚገቡ ዝሆኖችን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል ስላልታወቀ ሀሳቡ ብዙኀኑን አላስማማም።

130,000 ዝሆኖች ያሏት ቦትስዋና ዜጎቿ በዝሆኖቹ መኖር ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን ትናገራለች። የቦትስዋና ፕሬዘዳንት ለሦስቱ የአፍሪካ መሪዎች ከዝሆን እግር የተሠራ ዱካ ስጦታ የሰጡትም የእንስሳት ጥርስና ቀንድ ሽያጭን እንደሚደግፉ ለማሳየት ነው።

ባለፈው ዓመት ስልጣን የያዙት ፕሬዘዳንቱ ለዝሆኖች ጥበቃ የሚያደርግ ሕግን ማላላታቸው ይታወሳል።

የዝሆን አደንን መፍቀድ ወይም መከልከል በሀገሪቱ ለምርጫ ቅስቀሳ ከሚቀርቡ ሀሳቦች አንዱ ነው።

ናሚቢያ፣ ደቡብ አፍሪካና ዚምባብዌ አደን የሚፈቀድባቸው ሀገሮች ናቸው። የእንስሳት ጥርስና ቀንድ ሽያጭን የሚቃወሙ ሀገሮች በበኩላቸው ከዓመታት በፊት የነበረው ንግድ ለሕገ ወጥ አደን መንገድ መክፈቱን ይናገራሉ።