አዲሷ የኖርዌይ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር "ያሻችሁን ብሉ፣ ጠጡ፣ አጭሱ" ማለታቸው አስወገዛቸው

የኖርዌይ ጤና ጥበቃ ሚንስትር

የፎቶው ባለመብት, AFP

ኖርዌይ የጤና ጥበቃ ሚንስትር አድርጋ የሾመቻቸው ግለሰብ ዜጎች የፈለጉትን ያህል ይብሉ፣ ይጠጡ፣ ያጭሱ በማለታቸው መነጋገሪያ ሆነዋል።

ሲልቪያ ሊስታውግ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ተደርገው የተሾሙት አርብ እለት ሲሆን፤ አጫሾች መገለል እንዲሰማቸው ሲደረጉ መኖራቸውንም ተናግረዋል።

እኚህ ልወደድ ባይ ናቸው የተባሉት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በፀረ ስደተኛ አቋማቸው ይታወቃሉ። ከዓመት በፊትም ከነበራቸው የመንግሥት ኃላፊነት የወረዱት የሀገሪቱን ደህንነት ስጋት ውስጥ የሚጥል ውሳኔ ደግፈዋል በሚል በቀረበባቸው ተቃውሞ ነበር።

የሚኒስትሯን ሃሳብ የሚያብጠለጥሉ ግለሰቦች፤ ስለ ማህበረሰብ ጤና አንድም እውቀት የላቸውም ሲሉ ይኮንኗቸዋል።

ሚኒስትሯ ግን ለሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ምላሽ ላይ "የማህበረሰብ ጤና እውቀት የላትም ለሚለው ውንጀላ ያለኝ መልስ ቀላል ነው። የሞራል ልዕልናን ለማስጠበቅ የምቆም ፖሊስ ሆኜ ሰዎች ህይወታቸውን እንዴት መኖር እንዳለባቸው ለመንገር አልሞክርም። ነገር ግን ሰዎች መረጃ አግኝተው የራሳቸውን ውሳኔ እንዲወስኑ አደርጋለሁ" ብለዋል።

አክለውም "ዜጎች የሚፈልጉትን ያህል እንዲያጨሱ፣ እንዲጠጡ እና ስጋ እንዲበሉ መፈቀድ አለበት፤ ዜጎች የትኛው ጤናማ እንደሆነና እንዳልሆነ ያውቃሉ፤ ባለስልጣናት የሚጠበቅባቸው መረጃ መስጠት ብቻ ይመስለኛል" ብለዋል።

ሚኒስትሯ ከዚህ ቀደም አዘውትረው ያጨሱ የነበሩ ሲሆን አሁን ግን አልፎ አልፎ ብቻ እንደሚያጨሱ ይናገራሉ።

"የሚያጨሱ ሰዎች እንዲሸማቀቁ፣ ተደብቀው እንዲያጨሱ ይደረጋል፤ ይህ ረብ የለሽ ነው። ማጨስ ጤና ቢጎዳም ግለሰቦች ይህንን መወሰን ያለባቸው ራሳቸው ናቸው። እንደ መንግሥት ማድረግ ያለብን መረጃ መስጠት ብቻ ነው" ሲሉም አቋማቸውን ግልፅ ያደርጋሉ።

ግለሰቧ ከዚህ ቀደም በሽብር ተግባር የተጠረጠሩ ግለሰቦች የኖርዌይ ዜግነታቸውን እንዲነጠቁ የሚፀድቅ ሕግ ሲፀድቅ በመቃወማቸው የተነሳ ከሀገሪቱ ደህንነት ይልቅ "ለአሸባሪዎች መብት" ቆመዋል በሚል ከነበራቸው ኃላፊነት እንዲነሱ መደረጋቸው እታወቃል።