በአሜሪካ በግድያ የሚፈለገው ዮሃንስ ነሲቡ ተላልፎ ተሰጠ

ዮሃንስ ነሲቡ

የፎቶው ባለመብት, Fairfax County Police Department News

የምስሉ መግለጫ, ዮሃንስ ነሲቡ

በአሜሪካን ሃገር በሁለት ሰዎች ግድያ ክስ የተመሰረተበት እና በኢትዮጵያ ተሸሽጎ የነበረው ዮሃንስ ነሲቡ ለአሜሪካ መንግሥት ተላልፎ ተሰጠ።

በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት የፌርፋክስ ፖሊስ ዮሃንስ ነሲቡ ትናንት አሜሪካ መድረሱን በድረ-ገጹ አስታውቋል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በቨርጂኒያ ግዛት ፌርፋክስ ካውንቲ ፍርድ ቤት በሁለት ሰዎች ግድያ እና ያለ አግባብ የጦር መሳሪያ መጠቀም በሚሉ ወንጀሎች ክስ የተመሰረተበትን ዮሃንስ ነሲቡን አሳልፎ ለመስጠጥ ስለመወሰኑ መዘገቡ ይታወሳል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ እና የአሜሪካ ፖሊስ እንደሚሉት ዮሃንስ ነሲቡ በዛብህ የተባለው ግለሰብ፤ ከሁለት ዓመታት በፊት በአሜሪካን ሃገር ሁለት ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ገድሎ ወደ ኢትዮጵያ በማምለጥ ተጠርጥሯል።

''ዮሃንስ ነሲቡ በዛብህ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሲሆን የአሜሪካ ዜግነት አለው። የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ ተጠርጣሪው ከጥቂት ዓመታት በፊት በአሜሪካ ፈጽሞታል ተብሎ ለተጠረጠረበት የሁለት ሰዎች ግድያ እና በሁለት ያለ አግባብ የጦር መሳሪያ መጠቀም በሚሉ ወንጀሎች፤ በድምሩ በአራት ወንጀሎች እንደሚፈለግ ጠቁመው ተጠርጣሪው ተላልፎ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ጥያቄ ባቀረቡበት ሰነድ ላይ ወደፊት ኢትዮጵያ ለሚኖራት ተመሳሳይ ጥያቄ አሜሪካ ተባባሪ እንደምትሆን ገልጸዋል።'' በማለት ዮሃንስ ነሲቡ ተላልፎ እንዲሰጥ ስለመወሰኑ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህዝብ ግነኙነት ኃላፊ አቶ ዝናቡ ቱኑ ያብራራሉ።

ሄኖክ ዮሃንስ እና ቅድስት ስሜነህን

የፎቶው ባለመብት, Fairfax County Police Department News

የምስሉ መግለጫ, ሄኖክ ዮሃንስ እና ቅድስት ስሜነህ

የፌርፋክስ ካውንቲ ፖሊስ ዲፓርትመንት እንደሚለው ከሆነ የ24 ዓመቱ ዮሃንስ ነሲቡ ታህሳስ 7/2009 ዓ.ም. እና ታህሳስ 8/2009 ዓ.ም. ባሉት ተከታታይ ቀናት ትውልደ ኢትዮጵያዊ እና የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን የ22 ዓመት ወጣቶች ሄኖክ ዮሃንስ እና ቅድስት ስሜነህን በጥይት መትቶ በመግደል ተጠርጥሯል ይላል።

የአሜሪካ ፖሊስ እንደሚለው ከሆነ መረጃዎች ወደ ተጠርጣሪው ከመጠቆማቸው በፊት ዮሃንስ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ሸሽቷል።

ተጠርጣሪው ዮሃንስ ነሲቡ ለአሜሪካ መንግሥት ተላልፎ በመሰጠቱ ''የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያን የደህንነት ቢሮ፣ ፌደራል ፖሊስ እና የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግን ለትብብሩ እና ሙያዊ ተግባር ያመሰግናል'' ያለው የፌርፋክስ ካውንቲ ፖሊስ ዲፓርትመንት ነው።