የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የአውሮፓ ጉብኝት

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የአውሮፓ ቆይታቸው እንደቀጠለ ሲሆን የዓለም ምጣኔ ሃብት ፎረም ላይ ለመሳተፍ ሲዊትዘርላንድ ዳቮስ ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ እንስካሁን በነበራቸው ጉብኝት ከተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤዝሊ ጋር ተገናኝተዋል።

በሁለተኛው ቀን የአውሮፓ ጉብኝታቸው ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ ፕሬዝዳንት ጊልበርት ሆዉንግቦ ጋር ውይይት አድርገዋል።

ጠ/ሚር ዐብይ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በነበራቸው ቆይታ የመስኖና የምግብ ዋስትና እንቅስቃሴዎችን ማጠናከር ላይ በማተኮር እገዛ የሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎት ለማሟላት በመካከለኛ ደረጃ የመስኖና የገጠር ፋይናንስ ፍሰትን ለማጠናከር ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጽ/ቤታቸው አስታውቋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚንስትሩ ከጣሊያን ፕሬዝዳንት ሰርየጎ ማታሬላን፣ ከሮም ከንቲባ እና ከሮማው ጳጳስ ጋር ተገናኝተዋል።

የጣሊያን ቆይታቸውን ባጠናቀቁበት ትናንት ምሽት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥተዋል። ሁለቱ መሪዎች በሰጡት መግለጫ የበርካቶችን ቀልብ ስቦ የነበረው ከምፅዋ እስከ አዲስ አበባ ይዘረጋል የተባለው የባቡር መስመር ግንባታ ላይ ጣሊያን በሚኖራት ተሳትፎ ነበረ።

በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ምን ተባለ?

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ምፅዋን ከአዲስ አበባ በባቡር መስመር ለማገናኘት የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዩሴፔ ኮንቴ ፍላጎት አሳይተዋል ብለዋል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጨምረውም የባቡሩን መስመር ግንባታ አዋጪነት ጥናት ሙሉ ወጪ የመሸፈን ዝግጁ እንደሆኑም ጠቅሰዋል።

የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ በበኩላቸው ከጥቂት ወራት በፊት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ ጉብኝቱ ጣሊያን በአፍሪካ ቀንድ ላይ ትኩረት እንድታደርግ እረድቷታል ብለዋል።

በኢትዮጵያ፣ ኤርትራና በሶማሊያ መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ተቋማዊ በማድረግ በኩልም ጣሊያን በቋሚነት ተሳታፊ እንድትሆን እንመኛለን ብለዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከዳሰሷቸው ሌሎች ጉዳዮች መካከል በአዲስ አበባ ሰፊ መሬት ይዘው የሚገኙ ኤምባሲዎች ከፊሉን ክፍት በማድረግ የመናፈሻ አገልግሎት ለህዝብ እንዲሰጡ ፍላጎታቸው እንደሆነ ተናግረው ነበረ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የጣሊያን መንግሥት በአዲስ አበባ ያለውን የጣሊያን ኤምባሲን ለሕዝብ ክፍት ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።