አቶ ኤርሚያስ አመልጋ የዋስ መብታቸው እንዲከበር ጠየቁ የሚሉና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች

ኢትዮጵያ

የአክሰስ ሪል ስቴትና የዘመን ባንክ መስራች አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ከኢምፔሪያል ሆቴል ግዢ ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ የዋስ መብታቸው እንዲከበር ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በምላሹ 10 ቀን ለምርመራ ያስፈልገኛል ብሏል።

ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ የጉዞ አድዋ ተጓዦችን በዛሬው እለት የሸኙ ሲሆን "በእናንተ ውስጥ የትናንት ጀግና አባት እናቶች ይታዩኛል" በማለትም ለወጣቶቹ ተናግረዋል።

ለአገራቸው የ52 ዓመታት የዲፕሎማሲ አገልግሎት የሰጡት አምባሳደር ቆንጂት ስነ ጊዮርጊስ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ትናንት ለአንጋፋዋ አምባሳደር እውቅናና ሽልማቱን ያበረከቱላቸው ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ናቸው።

በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ የነዳጅ እጥረት ተከስቶ የትራንስፖርት መስተጓጎል ተከስቷል። እጥረቱ የተከሰተው ባለፉት ቀናት መንገዶች በተቃውሞ መዘጋታቸው ነው የሚል ጥርጣሬን አሳድሯል። ከመንግሥት በኩል እስካሁን ምላሽ አልተሰማም።

አሜሪካ

ኤርዶጋንና ትራምፕ በቃላት መወነጃጀላቸውን የቀጠሉ ሲሆን ትራምፕ ቱርክ በኩርዶች ላይ እጇን ታነሳና አይቀጡ ቅጣት እንቀጣታለን ማለታቸው የኤርዶጋንን መንግሥት አስቆጥቷል።

እንግሊዝ

የእንግሊዝና የአውሮፓ ህብረት መጨረሻ ዛሬ ይወሰናል። ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከአውሮፓ ኅብረት ፍቺ ለመፈጸም የገቡት ስምምነት እንደራሴዎቻች እንዲያጸድቁላቸው ላይ ታች ማለት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

ኬንያ

በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ የሚገኘው ቅንጡ ሆቴል ላይ ለተፈጸመው የሽብር ጥቃት አልሸባብ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ አለ። የአልሸባብ ቃል አቃባይ ጨምሮም ''በናይሮቢ ኦፕሬሽን እያካሄድን ነው'' ብሏል።

በዱሲት ሆቴል በደረሰው ጥቃት በርካታ ሰዎች ቆስለዋል።አንድ ሰው ሞቷል። ከአምስት አመት በፊት አልሸባብ ተመሳሳይ ጥቃት ሰንዝሮ 67 ሰዎች ተገድለው እንደነበር ይታወሳል።

ህንድ

በሕንድ 120 ሚሊዮን የሂንዱ አማኞች ሊጠመቁ ነው። አማኞች በየዓመቱ በጋንጀስና ያሙና ወንዞች የጥምቀት መንፈሳዊ ተግባርን ይፈጽማሉ።

ሳኡዲ አረቢያ

ካናዳ ያስጠለለቻት የ18 ዓመቷ አልቁኑን ሳኡዲ ሴቶችን ገረድ ታደርጋለች ስትል ተናገረች። አልቁኑን ለቶሮንቶ ስታር እንደተናገረችው ሳኡዲ አረቢያ እኛ ሴቶችን እንደ እቃ እንጂ እንደ ሰው ቆጥራን አታውቅም ብላለች።

አይቮሪኮስት

አለም አቀፉ ፍርድ ቤት የአይቮሪኮስትን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሎረን ባግቦን በነጻ አሰናብቷቸዋል። ባግቦ ላለፉት ሰባት ዓመታት እስር ላይ ነበሩ።