ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በዚምባብዌ ተቃውሞ አስነሳ
የዚምባብዌ መንግሥት የነዳጅ ዋጋ ከእጥፍ በላይ ከጨመረ በኋላ በተነሳው ተቃውሞ ሳቢያ ብዙ ሰዎች ተገድለዋል።
በሀራሬ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ አደባባይ የወጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል። ተቃዋሚዎቹ የመኪና ጎማ በማቃጠልም መንገድ ዘግተዋል።
የሀገሪቱ የደህንነት ሚንስትር ኦወን ንኩቤ የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን ቢያረጋግጡም በቁጥር አላስቀመጡም። ከተቃውሞው ጀርባ ባሉት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ ምርመራ ይጀመራል ብለዋል።
የዚምባብዌ ፕሬዘዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ እንዳሉት፤ የነዳጅ ዋጋ የተጨመረው የነዳጅ እጥረት ስለገጠመ ነው። እጥረቱ ያጋጠመው ደግሞ ሕገ ወጥ የነዳጅ ዝውውር እየተበራከተ በመምጣቱ ነው ብለዋል።
ሀራሬ ውስጥ የሚገኙ የንግድ ተቋሞች ለሦስት ቀናት የሥራ ማቆም አድማ እንዲያደርጉ የነጋዴ ማኅበራትና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አሳስበዋል።
የዚምባብዌ መንግሥት እየተንገታገተ ያለውን የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ፈር ለማስያዝ እየተጣጣረ ነው። ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ባያገኙም የዋጋ ንረት ኪሳቸውን እየፈተሸ መጥቷል።
የበርካታ ተቋማት ምርት ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር እየተጣጣመ አይደለም። የውጪ ምንዛሬ እጥረትም ሀገሪቱን ቀውስ ውስጥ ከቷታል።
ፕሬዘዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ፤ የነዳጅ እጥረት መከሰቱን በመጠቀም ሀገሪቱን አለመረጋጋት ውስጥ የሚከቱትን አንታገስም ብለዋል።
ከዚህ በተቃራኒው ቀዳሚው የሀገሪቱ የነጋዴዎች ማኅበር 'ዚምባብዌ ኮንግረስ ኦፍ ትሬድ ዩኒኢየንስ'፤ መንግሥት ለአቅመ ደካሞች ርህራሄ እያሳየ አይደልም ሲል ወቅሷል።
በርካታ ተቃዋሚዎች ፕሬዘዳንቱ ሀገሪቷ ለገጠሟት ችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጡ እየጠየቁ ነው። "ምናንጋግዋ ምንም ውጤት አለማምጣቱ እንዳበሳጨን እንዲያውቅ እንፈልጋለን" ሲሉ አንድ ተቃዋሚ ተደምጠዋል።
የሀገሪቱ ቀንደኛ ተቃዋሚ ፓርቲ 'ሙቭመንት ፎር ዴሞክራኣቲክ ቼንጅ' መሪ ኔልሰን ቻሚሳ፤ "ሀገር አቀፍ ቀውስ ውስጥ ነን፤ ይህም ሕዝቡን ፈተና ውስጥ ይከታል" ብለዋል።
ሮበርት ሙጋቤ ከሥልጣን ሲወገዱ ፕሬዘዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ የተኳቸው እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 ነበር። አምና የተካሄደው የዚምባብዌ ሀገር አቀፍ ምርጫ ከፍተኛ ውዝግብ ቢፈጥርም፤ ምናንጋግዋ አሸንፈው ሥልጣን ጨብጠዋል።