ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ለውጡን ማስቀጠል ተቋማዊ መሰረት እንደሚያስፈልገው ገለፁ
ዛሬ የጋራ 5ኛ ዘመን 4ኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ጉባኤን በንግግር የከፈቱት የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ስለ 2010 ዓመት አፈፃፀምና የመንግሥት ቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎችን በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል።
"መንግሥት ሰላምና የተረጋጋ ሀገር መፍጠርና በዚህ ሁኔታ ማስቀጠል የሚችለው የተሟላ የዲሞክራሲ ስርዓት ሲፈጠር ነው ብሎ ያምናል" ብለዋል።
በሀገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ለውጦችን እንደ ጥሩ እመርታ በማየት ይህንን ለማስቀጠል የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ተቋማዊ መሰረት እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።
የፍትህና የዴሞክራሲን ስርዓት ለማበልፀግም ሚና የሚኖራቸው ተቋማትን፣ ህግጋትንና አዋጆችን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ በዚህም መሰረት ልዩ ትኩረት የሚሰጥባቸውን ጉዳዮችን ጠቁመዋል። "የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ተቋማዊ መሰረት ከሌለው ረዥም መንገድ ሊጓዝ እንደማይችል ግልፅ ነው" ብለዋል።
መንግሥት የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበርና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ በማለምም በርካቶችን ከእስር መፍታት፤ እንዲሁም ለዓመታት ነፍጥ አንስተው ሲታገሉ ከነበሩ ኃይሎች ጋር ድርድር መጀመራቸውን እንደ ትልቅ እርምጃ በማንሳት በቅርቡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀው የምህረት አዋጅንም መንግሥት በዚህ ረገድ እየሄደ ያለበት አቅጣጫ አመላካች እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የዴሞክራሲ ስርዓቱ እንዲያብብና የተጀመሩ ማሻሻያዎችም በዘላቂነት ተቋማዊ መሰረት እንዲኖራቸው ለማድረግም አማካሪ ኮሚቴ መቋቋሙንም ገልፀዋል። አማካሪ ኮሚቴው በቴክኒክ ኮሚቴ የሚታገዝ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልፀው በዚህ ዓመትም የፀረ-ሽብር አዋጅ፣ የሲቪክ ማህበራትና በጎ አድራጎት ማህበር አዋጅ፣ የመገናኛ ብዙኃን እና የመረጃ ነፃነት አዋጅን ጨምሮ ሌሎች አዋጆችን የማሻሻል ስራ ይሰራል ብለዋል።
በንግግራቸው ከለውጥና ከማሻሻያ ሂደት ጋርም በተገናኘ የፖለቲካ ምህዳርን ስለ ማስፋት፣ በዓመቱ ያጋጠመውን የምጣኔ ኃብት ነክ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ስለ መውሰድ፣ ዲፕሎማሲ፣ ቀጠናውንም ሆነ አህጉሪቷን እንዴት በንግድ ማስተሳሰር ይቻላል የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮችንም በንግግራቸው ዳሰዋል።
ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከርም ከ2011 ጀምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ የመዳረሻ ቪዛን ለመስጠትና እቅድ እንዳለ ገልፀው በተለይም ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና ከመሆኗም ጋር ተያይዞ ትስስሩን እንደሚያጠናክርና ከቦታ ቦታ መዘዋወርንም ለማቅለል እንደሚረዳ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን በትኩረት ይሰራል ብለዋል።