ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ
በሀዋሳ ከተማ ሲካሄድ በነበረው የኢህአዴግ 11ኛ መደበኛ ጉባኤ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የድርጅቱ ሊቀ መንበር ሆነው በድጋሚ ተመረጡ።ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከጠቅላላው 177 ድምፅ 176ቱን በማግኘት እንደተመረጡ ታውቋል።
አቶ ደመቀ መኮነን ደግሞ በ149 ድምፅ ም/ሊቀመንበር ተደርገው ተሹመዋል። ለምክትል ሊቀመንበርነት በእጩነት የቀረቡት ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል በበኩላቸው 15 ድምፅ አግኝተዋል።
የምርጫው አሰጣጡ ሂደት በ12 የኮሚቴ አባላት የተመራ ሲሆን፤ በአቶ ብርሃኑ ፀጋዬ አስመራጭ ኮሚቴ መሪነት እና በወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ምክትል መሪነት ተካሄዷል።
በተጨማሪም በዕለቱ የድርጅቱ የቁጥጥር ኮሚቴ ተቋቁሟል። ኮሚቴው በአቶ አወቀ ኃይለማሪያም መሪነት፣ በአቶ ጀማል ረዲ (ደኢህዴን) ምክትል ኃላፊነትና በአቶ ብርሃኑ ፈይሳ (ኦዴፓ) ፀሐፊነት እንደሚመራ ተገልጿል።
የኢህአዴግ ጉባኤ ነገ ማለዳ በሀዋሳ ስቴዲየም በሚደረግ ስነ ስርዓት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።