እንወራረድ፡- የጦፈው የውርርድ ንግድ በአዲስ አበባ

ቀን ሲሰጥ ውርርድ ያልታሰበ ሲሳይ ያመጣል፡፡

ቀን ሲጥል ደግሞ በአንጻሩ ላልተፈለገ ዕዳ ይዳርጋል፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የስፖርት ውርርድ ቤቶች ቤተኛ የነበረው ናትናኤል ተክሉ ልምድ የሚነግረንም ይሄንኑ ነው፡፡

"አራት መቶ ብር አስይዤ ፣11 የሚሆኑ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ውጤት ቀድሜ በመተንበይ 34ሺ ብር አሸንፌ አውቃለሁ፡፡"ሲል የፍስሃ ዘመኑን የሚያስታውሰው ናትናኤል በሌላ ጊዜ 5000ሺ ብር "የተበላበትን" ውርርድ ሲያስታውስ እንደሚቆጨው ድምጹ ያሳብቃል፡፡

ውርርድ እንዲህ ጽንፍ እና ጽንፍ ላይ ከቆሙ ስሜቶች ጋር በፍርርቅ የሚላተም "ጨዋታ" ነው፡፡

ያም ቢሆንም ቅሉ በዛሬዋ አዲስ አበባ ህጋዊ ንግድ ከመሆን አልገታውም፡፡ ከብሄራዊ ሎተሪ ፈቃድ አግኝተው የሚንቀሳቀሱ 10 ያህል የውርርድ ድርጅቶች በአዲስ አበባ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ መካከል አንዱ ሀበሻ ስፖርት ውርርድ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው፡፡

ከ20 በላይ ቅርንጫፎች ባሉት በዚህ ድርጅት ስር የስፖርት አፍቃሪያን ከሁለት ቡድኖች (ተፎካካሪዎች) መካካል የቱ እንደሚያሸንፍ፣በምን ያክል የጎል መጠን እንደሚረታ ፣እና የመሳሰሉ ሁነቶች ቀድመው በመገመት ብሎም ገንዘብ በማስያዝ ከድርጅቱ ጋር ይወራረዳሉ፡፡

ተጫዋቾች ከ10ብር ጀምረው መጫዎት እንደሚችሉ የሚናገሩት የድርጅቱ ሃላፊ አቶ የኔ ብልህ ባንተ አየሁ እስከ 350ሺ ብር ድረስ ደግሞ ማሸነፍ ይችላሉም ይላሉ።

ብዙ ጊዜ ለውርርድ የሚመረጠው ስፖርት እግር ኳስ፤ ከእግር ኳስም የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

ስፖርታዊ ውርርድ ስሜታዊነት የሚያጅበው ጨዋታ ነው፡፡መጨረሻው ገንዘብ ማግኘት ወይ ገንዘብ ማጣትን የሚያስከትል እንደመሆኑ ለድርጅቶችም ለተጫዋቾችም የሚተወው ራስ ምታት አይናቅም፡፡

አቶ የኔ ብልህ እሳቸው ያዩዋቸውንም ሲገልጹ "ግጭቶች ይፈጠራሉ፡፡ማዘን ይፈጠራል፡፡የተለያዩ ውዥንብሮችም ይከተላሉ፡፡ተጫዎቾቹ ‹ብናሸንፍ ድርጅቱ ቃል የገባውን ገንዘብ ይሰጠናል ወይ!" የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡

የተሸነፉ ተወራራጆች "ማስተዛዘኛ የሚሆን ነገር ልናገኝ ይገባል!'የሚል ጥያቄም ያቀርባሉ፡፡እኒህን ችግሮች የጨዋታውን ህግ እና ደንብ በማስረዳት ለመቅረፍ ሞክረናል፤" ይላሉ፡፡

በቅርቡ ከስፖርታዊ ውርርዶች ራሱን ያራቀው ናትናኤል ተክሉ ውርርድ የሚፈጥረው ስሜታዊነትን የሚገነዘበው ለተወራራጆች ከሚፈጥረው ጤናማ ያልሆነ ጥንዎት አንጻር ነው፡፡

ተወራራጆች ከጊዜያት በኋላ በረቡ ባልረቡ ጨዋታዎች ላይ ሳይቀር ተጠምደው ገንዘባቸውን ሲያፈሱ እንደሚያስተውል የሚነሳው ናትናኤል ፣ስሜቱ ልጓም ካልተበጀለት የተጨዋቾችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህልውና ከማናጋት እንደማይመለስ ይጠቁማል ፤"እንደ ቁማር ሁሉ ሱስ ያስይዛል፡፡

አንድ ሱሰኛ ማናቸውም ነገሮችን በማድረግ ሱሱን ለማሟላት እንደሚጥረው ሁሉ ይሄንንም የውርርድ ሱስ በየትኛውም መንገድ ለማስታገስ (ብዙ ርቀት )የሚሄዱ ሰዎች እንዳሉም ይናገራሉ።

የሀበሻ ስፖርት ውርርድ ድርጅት ሃላፊ አቶ የኔ ብልህ በበኩላቸው ውርርድ በመዝናኛ አማራጭነቱ እና እየፈጠረ ባለው የስራ ዕድል ላይ ያተኩራሉ፡፡

ለዋቢነት የሚያቀርቡት ደግሞ በድርጅታቸው ስር ተቀጥረው የሚሰሩ ከ70 በላይ ወጣት ሰራተኞችን ነው፡፡

የሆነው ሆነና አዲስ አበባ ስፖርታዊ ውርርድ ደርቶባታል፡፡ግዙፍ ቴሌቭዥኖችን ላይ ዐይናቸውን የተከሉ ተወራራጆች እዚህም እዚያም ማየት ብርቅነቱ ቀርቷል፡፡

በለስ የቀናቸው በደስታ ይፈነጥዛሉ፡፡ያልተሳካላቸው ጸጉራቸውን ይነጫሉ፡፡እንዲህ እንዲህ እያለ ውርርዱ ይቀጥላል፡፡