በአማራ ክልል ከ4500 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ

በአማራ ክልል ከ4ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የጸጥታ ቢሮው ዛሬ ግንቦት 15/2014 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከሰሞኑ መንግሥት ያካሄደውን "የሕግ ማስከበር ዘመቻ" ተከትሎ መሆኑን አመልክቷል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት አጠቃላይ ተጠርጣሪዎች ብዛት 4 ሺህ 552 እንደሆነና ከእነዚህ ውስጥ 210 የሚሆኑት በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ምርመራ ተጣርቶባቸው የተከሰሱና በሕግ ጥላ ስር ማድረግ ሳይቻል የቆዩ መሆናቸው ተገልጿል።

ከ40 በላይ የሚሆኑት የወንጀል ፍርደኞች ሆነው ከማረሚያ ቤት ያመለጡ፣ ከ39 በላይ የሚሆኑት ወንጀለኞች ሆነው በሌሉበት የተፈረደባቸው፣ 917 ግለሰቦች ደግሞ "በጽንፈኞች እና የክልሉ ጠላቶች ተልዕኮ የተሰጣቸው" መሆናቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም "ፀጉረ ልውጦችን ጨምሮ በፀጥታ እና መንግሥት መዋቅር ሆነው ለወንጀል ተባባሪነት" የተጠረጠሩ ከ1 ሺህ 780 በላይ ግለሰቦች እንደሚገኙበት ታክሏል።

የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው የአማራ ክልል "ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል" ማለታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። አቶ ደሳለኝ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ከሚደርገው ሥራ ውጭ "ክልሉ አስተማማኝ ሰላም ላይ ነው" ማለታቸውም ተዘግቧል።

እንደ አገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ከሆነ፣ "ትክክለኛውን የፋኖ ስም የማይወክሉ፣ በፋኖ ስም ተደራጅተው በሕዝብ ላይ የተለያዩ ሕገ ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ቡድኖችን መንግሥት እንደማይታገስም" ብለዋል።

አቶ ደሳለኝ በመግለጫቸው፣ "የመንግሥትን የማድረግ አቅም እና የሕግ የበላይነትን በመፈታተን በክልሉ ሥርአት አልበኝነት እንዲነግሥ" አድርገዋል በተባሉት ግለሰቦች ምክንያት "መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብትን፣ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ" እንደተቸገረም ጠቁመዋል።

ባለፈው ሳምንት የአማራ ክልል በግለሰቦች እጅ የሚገኝ የጦር መሣሪያ ምዝገባ ሊካሄድ መሆኑን የክልሉ የሰላምና የፀጥታ ቢሮ ማስታወቁን ተከትሎ ክልሉ "የሕግ ማስከበር ዘመቻ" መጀመሩን አስታውቋል።

በተለይም በበርካታ አካባቢዎች በስፋት በተደራጀው ፋኖ በተባለው መደበኛ ያልሆነ ታጣቂ ቡድን "ስም ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ግለሰቦችና ቡድኖች" ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ መገለጹ አይዘነጋም።

የፀጥታ ኃይሎች "ሕግ ማስከበር" ያሉትን እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተከሰቱ ግጭቶች በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎችና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በምሥራቅ እና በምዕራብ ጎጃም በሰሜን ወሎ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ሳቢያ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ሕይወት ማለፉንና የአካል ጉዳት መድረሱን መዘገባችን ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ግንቦት 14/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የፌዴራል መንግሥት እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች "በተቀናጀ መንገድ የሕግ የበላይነትን ማስከበር" በሚል ባለፉት ጥቂት ቀናት መውሰድ በጀመሩት እርምጃ "ጋዜጠኞችና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ታስረዋል" ብሏል።

ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ውስጥ መሰወራቸው የተነገረው የቀድሞው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ፣ "ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ" ሞክረዋል በሚል ተጠርጥረው እንደተያዙና በባለፈው ሳምንት ማገባደጃ በባሕር ዳር ጠቅላይ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ይታወሳል።

በማኅበራዊና በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ የኢትዮጵያን መንግሥት በመተቸት የምትታወቀው መስከረም አበራ ቅዳሜ ግንቦት 13/2014 ዓ. ም. በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር መዋሏን ባለቤቷ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ጦርነቱን በመቃወም እንዲሁም የሰላምና ድርድር መንገዶች የተሻሉ አማራጮች እንደሆኑ በተደጋጋሚ አፅንኦት በመስጠት የሚታወቀው ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬም መታሰሩ ተዘግቧል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ዘጠኝ አባላትም ግንቦት 10/2014 ዓ. ም. በሁለት ከተሞች መታሰራቸውን ሮይተርስ በአሜሪካ የሚገኘውን የአማራ ማኅበር ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።