ሩሲያዊው ወታደር ብስክሌት እየጋለቡ የነበሩትን ዩክሬናዊ ሽማግሌ ተኩሶ መግደሉን አመነ

የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በቀጠለበት በዚህ ወቅት የ21 ዓመቱ የሩሲያ ወታደር በዩክሬን ፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡

ሩሲያዊው ቫዲም ሺሺማሪን የ62 ዓመት ሽማግሌ ዩክሬናዊን በጭካኔ መግደሉን አምኗል፡፡

ሟች ምንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ባልያዙበት ሁኔታ ነው ይህ ሩሲያዊው ወታደር በጭካኔ ተኩሶ እንደገደላቸው ለፍርድ ቤት የእምነት ክህደት ቃሉን የሰጠው፡፡

በዩክሬን ምድር ከጦርነቱ ወዲህ የሩሲያ ወታደሮችን ለፈጸሙት የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት ሲቀርብ ቫዲም የመጀመርያው ነው፡፡

ሩሲያዊው ወታደር ዕድሜ ይፍታህ ፍርድ ይጠብቀዋል ተብሏል፡፡

ሩሲያዊው ወታደር በዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ በሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረበው እጁ በሰንሰለት ታስሮ በጠንካራ የወታደሮች አጀብ ነበር፡፡

ፊቱ ላይ የመደናገጥ ስሜት ይነበብ ነበር፡፡ ፍርድን ሲከታተል የነበረውም አንገቱን አቀርቅሮ ነው፡፡

የሟች ባለቤት የነበሩት ሴት በፍርድ ቤቱ ጥግ ከባለቤታቸው ገዳይ በቅርብ ርቀት ተቀምጠው ፍርዱን ተከታትለዋል፡፡

ሴትዮዋ ተጠርጣሪው ሩሲያዊ ወታደር ወደ ፍርድ ቤት በገባበት ቅጽበት እንባቸውን ሲያብሱ ታይተዋል፡፡

ዳኛው የፍርዱን ፍሬ ነገር ካነበቡ በኋላ ለሩሲያዊው ወታደር፣ ‹‹ሰውዬውን እንደገደልካቸው ጥፋተኝነትህን ታምናለህ ወይ?›› የሚል ጥያቄ ያቀረቡለት ሲሆን፣ ሩሲያዊው ወታደር ‹አዎን ጥፋተኛ ነኝ፡፡›› ሲል መልሷል፡፡

‹‹እርግጠኛ ነህ?›› የሚል ጥያቄ የተከተለ ሲሆን ተጠርጣሪው ‹‹አዎን እርግጠኛ ነኝ›› ብሏል፡፡

ይህ ሩሲያዊ ወታደር የታንከኛ ቡድን አባል የነበረ ሲሆን እሱ የነበረበት ቡድን ላይ ጥቃት ሲከፈት ከአራት ሌሎች ወታደሮች ጋር በመሆን መኪና ሰርቀው በሽሽት ላይ ነበሩ፡፡

ቻፑኪቫክ የተባለ አካባቢ ሲደርሱ አንድ የ62 ዓመት ሰው በብስክሌት ሲጓዙ ተመለከተ፡፡

ይህ ሩሲያዊ ተጠርጣሪ በያዘው ክላሺንኮቭ መሣሪያ ሰውየውንም ገደላቸው ይላል አቃቤ ሕግ

የሟች ባለቤት የነበሩት ሴት ለቢቢሲ በባላቸው የግፍ ግድያ ልባቸው መሰበሩን እና ጥፋተኛውን ሩሲያዊ ወታደር መቼም ቢሆን ይቅር እንደማይሉት ተናግረዋል፡፡

ዩክሬን 10 ሺህ የሚሆኑ የጦር ወንጀሎች በሩሲያ መፈጸማቸውን ገልጻለች፡፡

የአገሪቱ ዋና አቃቢ ሕግ ኢርያን ቬኔዲክቶቫ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ እንደጻፉት ‹‹በዚህ የሩሲያ አንድ ወታደር የፍርድ ሂደት ልናስተላልፍ የምንፈልገው መልእክት ማንም ቢሆን ከሕግ እንደማያመልጥ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡

ሞስኮ ወታደሮቿ በንጹሐን ላይ አንዳችም ጥፋት አላደረሱም ስትል ታስተባብላለች፡፡

ዩክሬን የጦር ወንጀል ፈጽመዋል ያለቻቸውን የሩሲያ ወታደሮች ወደ ሄግ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለመውሰድ እየሠራች ነው፡፡

የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በበኩሉ 42 መርማሪዎችን ወደ ዩክሬን ለመላክ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡