ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መፍትሔ ያጣው ኬንያን ከኢትዮጵያ የሚያዋስነው የመርሳቤት ግዛት የፀጥታ ችግር
አቶ ሰላድ ጃርሶ፣ የ11 ዓመት ሴት ልጃቸው የምትማርበት ትምህርት ቤት ፊት ለፊት የተገደለችበትን ቀን በከባድ ሐዘን ውስጥ ሆነው ነው የሚያስታውሱት።
ሰሜን ኬንያ መርሳቤት ግዛት በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 5 2021 ነበር ዩኒፎርሟን እንደለበሰች በጥይት ተመትታ የተገደለችው።
የመርሳቤት ግዛት ከኢትዮጵያ ጋር 500 ኪሎሜትር የሚሸፍን ድንበር ይጋራል ይህም ከሞያሌ በስተምስራቅ በኩል እንዲሁም በቱርካና ሃይቅ በኩል እስከ ኢሊሬት ያሉ የኬንያ ግዛቶችን ይሸፍናል።
ኬንያና ኢትዮጵያ የሚዋሰኑበት የድንበር ግዛት ሰላም ካጣ ሰነባብቷል። ችግሩ እየበረታ ሲመጣም የኬንያ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ባልተለመደ መልኩ እርምጃ ለመውሰድ ተገድዷል።
በቅርቡ በግዛቱ በተቀሰቀሰ የጎሳ ግጭት ምክንያት በርካታ ሰዎች መገዳላቸውን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች እና የፀጥታ ኃይሎች ተሰማርተዋል።
በመርሳቤት ለተፈጠረው የፀጥታ ችግር መንስኤ ድርቅ፣ ፖለቲካዊ ቅስቀሳ እና በግጭት ከምትታመሰው ኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ በቀላሉ መገኘቱ ነው ሲል የኬንያ መንግሥት ገልጿል።
የኬንያ የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር ፖሊስ ከደቡብ ኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ የገቡ በርካታ የጦር መሳሪያዎችን እና ጥይቶችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን መናገራቸው ይታወሳል።
በግዛቱ ውስጥ ያለውን የፀጥታ ችግር እንዲሁም ደግሞ የሰው ሕይወት እና ንብረት የቀጠፈው ለመቆጣጠር ከግንቦት ወር ጀምሮ የሰዓት እላፊን በመደንገግ ርምጃ እየወሰደ ይገኛል።
በዚህም የተለያዩ የፀጥታ አካላትን ወደ ግዛቲቱ በማሰማራት ለመቆጣጠር እየጣረ ይገኛል። እርምጃውን ተንተርሶም የተሳካላትም ይመስላል።
የአገሪቱ መንግሥት በዚህ ግዛት ውስጥ በቦረና እና በገብራ ማኀበረሰብ መካከል ጥላቻ እና ግድያ እየተበባሰ በመምጣቱ ይህንን ርምጃ ለመውሰድ መገደዱን ይናገራል።
ኬንያና እና ኢትዮጵያ ረዘም ያለ 861 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው ድንበር ይጋራሉ። በኬንያ በኩል መርሳቤት፣ ቱርካና፣ ዋጂ እና ማንዴራ ግዛቶችን የሚያካትት ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል ቦረና እና ዳዋ አሉበት።
ማስጠንቀቂያ -እዚህ ታሪክ ውስጥ የተጠቀሱ ግድያዎች አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሹ ይችላሉ።
'የልጄን ቦርሳ መሬት ላይ ወድቆ አገኘሁት'
አቶ ሰላድ ሴት ልጃቸው ሰብዲዮ ከሞተች ወራት ቢቆጠሩም እለቱን ልክ አሁን የሆነ ያክል ያስታውሱታል።
እኚህ አባት የልጃቸውን ሞት የሰሙበትን አጋጣሚ እንዲህ ይተርካሉ።
"ትምህርት ቤት ሰው ገደሉ የሚል ወሬ ሰማሁኝ። በሊትል ኤንጅል ትምህርት ቤት ሶስት ሰው እንደተገደለ ነው የሰማሁት። ከአካባቢው ርቄ ስለነበር መኪና ይዤ ወደ ትምህርት ቤቱ እየከነፍኩ ሄድኩ። እዚያ ስደርስ ቤተሰብ ሁሉ ልጆቹን እየወሰደ ነበር። የልጄን ቦርሳ ትምህርት ቤቱ ፊት ለፊት ወድቆ አየሁት። የዛን ጊዜ የተገደለችው ሰብድዮ ብቻ ሳትሆን፣ በሞተር የሚያመላልሳት አጎቷ እና አንድ የጎረቤት ልጅም ጭምር መሆናቸውን ተረዳሁ።
"ሁለት አስክሬን ወድቆ ሳይ በጣም ደነገጥኩኝ። ልጄን ወደ ሆስፒታል እንደወሰዷት ስረዳ ጊዜ ሳላጠፋ ወደዚያው አመራሁ። ሆስፒታል ስደርስ የልጄን መሞት ተረዳሁ። እዚያው በከፍተኛ ድንጋጤ ተመታሁ። አስከሬኗን ወስደን በነጋታው ስርዓተ ቀብሯን ፈፀምን። ይሀው ከዚያን ግድያ በኋላ ሰብድዮ ትማርበት የነበረበው ሊትል ኤንጅልስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደተዘጋ ነው።"
ስለ ልጃቸው ባሕሪ ሲናገሩ "ከልጆቼ ሁሉ በጣም አይናፋር፣ እና ተወዳጅ ነበረች" ይላሉ።
ቢቢሲ ግድያው በፈፀመበት ስፍራ በተገኘበት ወቅትም ትምህርት ቤቱ ተዘግቶ እንዳለ ነው።
አቶ ሰላድም የልጃቸው ሰብድዮን የመቃብር ስፍራ ለቢቢሲ ጋዜጠኞች ወስደው ሲያሳዩ አይናቸው በእንባ ተሞልቶ እና ስሜታቸው ደፍርሶ ነበር።
ፍትሕ አላገኘሁም
የ11 ዓመት ሴት ልጃቸው ሰብድዮ ሰላድ መንገድ ላይ ጭካኔ በተመላበት ከተገደለች ዘጠኝ ወራት ቢቆጠሩም እስካሁን በዚህ ግድያ ምክንያት ተጠርጥሮ ሕግ ፊት የቀረበ አካል የለም።
"ይህች ልጅ ከተገደለች በኋላ የመንግሥት ሰዎች አንድ ወር ሙሉ አጥፊዎችን ሲፈልጉ ነበር። እኔ ሴት ልጄን ዩኒፎርም አልብሽያት ቦርሳ አስይዤ ትምህርት ቤት ልኬያት እነርሱ ገደሏት። ማን እንደገደላት አላየሁም። . . .የሰውን ሕይወትና ንብረት መጠበቅ ያለበት መንግሥት ነው። መንግሥት በተገቢው ሁኔታ ሥራውን አልተወጣም፤ መንግሥት አጥፊዎችን ተከታትሎ መያዝ አለበት።" ሲሉ በንዴት ይናገራሉ።
"ይህ ሰውዬ [የልጄ ገዳይ] እየበላ እየጠጣ ነው። ይህንን የሚያደርገው ሰው ትምህርት ቤት ልጁን የሚልክ ሰው አይደለም። እኔ እንዲህ ዓይነት ነገር በጭራሽ አይቼ አላውቅም" ሲሉ ስለ ጎሳ እና ስለ ፖለቲካ የማያውቁ ሕጻናት በጭካኔ መግደል ትልቅ ክፋት መሆኑን ያስረዳሉ።
". . . ተማሪዎችን፣ ስለ ጎሳ የማያውቁትን፣ የማን ጎሳ ነች ብለው ጠያይቀው፣ ሴት ልጆችን ይገድላሉ። በጣም ነው የተከፋሁት" ሲሉ አይናቸው በእንባ ተሞልቶ ይናገራሉ።
የኬንያ መንግሥት የፀጥታ ርምጃ
የኬንያ መንግሥት ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ በመርሳቤት ግዛት በሰው እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት ያደረሰውን የፀጥታ ችግር ለመቆጣጠር ከግንቦት ወር ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ የእንቅስቃሴ ገደብ በማስቀመጥ ርምጃም እየወሰደ ይገኛል።
ይህ የሰዓት እላፊ ለአንድ ወር የታወጀ ሲሆን፣ በአካባቢው የፀጥታ ችግር እንዲባባስ ምክንያት የሆኑት የጦር መሳርያዎች እስኪጠፉ ድረስ ሊቀጥል ይችላል በማለት የኬንያ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ፍሬድ ማቲያንጌ ገልፀዋል።
ይህ የሰዓት እላፊ ታውጆ ወደ ስራ ከተገባ ሁለት ሳምንት ያለፈ ሲሆን፣ |የአካባቢው ማህበረሰብም ስለ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ርምጃ የተደበላላቀ ስሜት እንዳላቸው ቢቢሲ መረዳት ችሏል።
ቢቢሲ ካነጋገርናቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ርምጃውን በመደገፍ "ሠላም ወረደ ሰው እየተገዳደለ አይደለም" በማለት በከተማይቱ የተሰማሩ የመንግሥት አካላትን በደስታ ሲቀበሉ ተመልክቷል።
ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ላይ ችግር ማስከተሉን በመግለጽ ቅሬታቸውን ያቀርባሉ።
በተለይ ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉ፣ ነጋዴዎች ላይ ጫና እንዳሳደረ በመግለጽ ምሬታቸውን ያቀርባሉ።
በተጨማሪም በግዛቲቱ የተሰማሩ የፖሊስ አባላት በሰበብ አስባቡ ነዋሪዎችን በመደብደብ እና ማንገላታት ይከሰሳሉ።
የሰገንቴ ጀልዴሳ አካባቢ አስተዳዳሪ አቶ ሶራ ከቴሎ "ፖሊሶች ወደዚህ መሰማራታቸው ገሚሱ እንደ መፍትሔ ያየዋል ገሚሱ ይከስሳቸዋል" ሲሉ ያለውን ሁኔታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ወታደራዊ ርምጃ መልካም ነገር አይደለም፤ የመጨረሻ አማራጭ ነው" በማለት የመንግሥት የፀጥታ አካላት ወደ አካባቢው ከተሰማሩ በኋላ ግድያ እንደቆመ ይናገራል።
በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ የፀጥታ አካላት በዘረፋ ይከሰሳሉ።
"23 ሺህ ሽልንግ ከአንድ ቤተሰብ ሰረቁ. . .150 ሺህ ሽልንግ ደግሞ ከአንድ እናት ላይ ወስደዋል" በማለት ይህንን ጉዳይ ለመንግሥት ማሳወቃቸውን ይነገራሉ።
አክለውም 'ሰው መቱ ሰው ሰባበሩ' በማለት ከተማይቱ ውስጥ እንቅስቃሴ መቆሙን እና እርሳቸውንም ጨምሮ በፖሊስ መመታታቸውን ይናገራሉ።
ልጃቸው የተገደለችባቸው አቶ ሰላድ በበኩላቸው " ወታደራዊ ርምጃው ከተጀመረ፣ ሰው የሚገድሉ ሰዎች ሸሽተዋል። ይህ ወታደራዊ ርምጃ ምስኪኖች መንገድ ላይ እየሄዱ ወታደሮች ይመቷቸዋል" ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።
ነዋሪዎች በፀጥታ አካላት ላይ ያቀረቡትን ቅሬታ በሚመለከት የኬንያን ፖሊስ ሃሳብ ለማካተት ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካም።