ፑቲን ፊንላንድ ኔቶን መቀላቀል መፈለጓ 'ስህተት ነው' ሲሉ አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፊንላንድ የኔቶ (የሰሜን አትላቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት) አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት እንድታቆምና ገለልተኛ መሆኗን ማቆሟ ትልቅ ስህተት እንደሚሆን የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስጠነቀቁ።
ለፊንላንዱ ፕሬዝዳንት ሳኡሊ ኒኒስቶ ባስተላላፉት መልዕክት ለፊንላንድ ደህንነት ምንም የሚያሰጋት ነገር እንደሌለና የኔቶ አባል መሆን እንደማይጠበቅባት ገልጸዋል።
ሁለቱ መሪዎች ንግግር ያደረጉት የፊንላንዱ መሪ ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመወያየት መጠየቃቸውን ተከትሎ በተደረገ የስልክ ንግግር ነው።
ስዊድንም ብትሆን ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ የኔቶ አባል የመሆን ፍላጎቷን በይፋዊ ጥያቄ አሳውቃለች።
ፊንላንድ 1300 ኪሎሜትር የሚረዝም ድንበሯን ከሩሲያ ጋር የምትዋሰንበት ሲሆን አገሪቱ የኔቶ አባል አገር ሳትሆን የቆየችውም ጎረቤት ሩሲያን ላለማስቆጣት ነው።
ፕሬዝዳንት ፑቲን የፊንላንድ እርምጃ ስህተት ትልቅ ምላሽ የሚያስከትል ነው ቢሉም በትክክል ግን ምን አይነት እርምጃ እንደሚወስዱ አልገለጹም።
ነገር ግን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሩሲያ ምላሽ እንደምትሰጥ አስታውቋል።
ሩሲያ ለፊንላንድ ታቀርበው የነበረውን የኤልክትሪክ ኃይል ማቋረጧ ደግሞ ቀዳሚ ምልክት ተደርጎ ተወስዷል።
የሩሲያው የኃይል አቅራቢ 'ራኦ ኖርዲል' እንዳለው አቅርቦቱ የተቋረጠው ከክፍያ ጋር በተያያዘ ነው።
ፊንላንድ ግን የኃይል አቅርቦቱ መቋረጥ እዚህ ግባ የሚባል ችግር እንዳላስከተለባት ገልጻለች። የአገሪቱ ብሄራዊ የኃይል ኃላፊው ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ''ሩሲያ ኃይል ማቋረጧ ምንም አይነት ችግር አልፈጠረብንም'' ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም ከሩሲያ የሚገባው የኃይል አቅርቦት ከአገሪቱ ፍላጎት 10 በመቶ የሚሆነውን ብቻ እንደሚሽፍንና በሌሎች አማራጮች ሊተካ እንደሚችል ገልጸዋል።
ሁለቱ መሪዎች ቅዳሜ ዕለት በስልክ ውይይት ካደረጉ በኋላ ክሬምሊን ባወጣው መገልጫ ፊንላንድ ከዚህ በፊት ትከተለው የነበረው ገለልተኛ አቋሟን ለመቀየር ማሰቧ ትልቅ ስህተት እንደሆነና ለደህንነቷም የሚያሰጋት እንደሆነ የሩሲያው መሪ ማሳሰባቸውን ገልጿል።
መግለጫው አክሎም '' አገሪቱ መሰል ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን ስትወስን በሩሲያና ፊንላንድ መካከል የነበረውን ወዳጅነት በእጅጉ ይጎዳዋል። ሁለቱ አገራት ለዓመታት የቆየ ወዳጅነት ጉርብትና መመስረት የቻሉ ናቸው'' ብሏል።
የፊንላንዱ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ የአገራቸው ደህንነት አደጋ ላይ መውደቁንና ይህ ደግሞ እንደሚያሰጋቸው ለሩሲያው ፕሬዝዳንት አስረድተዋል።
አክለውም '' ያደረግነው ንግግር ቀጥተኛና በትክከል ጉዳዩን ስለመፍታት ነበር። የተፈጠሩ ውጥረቶችን ማርገብ ደግሞ ወሳኝ እንደሆነ ተግባብተናል'' ብለዋል።
ፊንላንድና ሰዊድን የኔቶ አባል ለመሆን በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ሌላ ፈተና የሆነችባቸው ቱርክ ነች። ፕሬዝዳንት ራሲፕ ታይብ ኤርዶዋን ሁለቱ አገራት ሽብርተኞችን እየሸሸጉ እንደሆነና የኔቶ አባል ለመሆን ያቀረቡትን ጥያቄ እንደማይቀበሉት ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ምዕራባዊያን አገራት ሩሲያን እየከበቡ ነው ይላሉ። ኔቶ በምሥራቅ አውሮፓ ያለውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲያቆም ይፈልጋሉ።
አሜሪካ እአአ በ1990 ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ላለመስፋፋት የደረሰችውን ስምምነት ጥሳለችም ይላሉ። አሜሪካ ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ቃል አልገባሁም ስትል ትመልሳለች።
ኔቶ በበኩሉ ትንሽ ቁጥር ያላቸው አባል አገራቱ ከሩሲያ ጋር ድንበር እንደሚጋሩ ይገልጻል። ይህንንም ወታደራዊ ጥምረት ነው ሲል ይገልጸዋል።












