በኢትዮጵያ ጦርነት እንዲያበቃ ከሁለቱም ወገኖች ጋር ግንኙነት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጉቴሬዝ ተናገሩ

በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት እንዲያበቃ ከሁለቱም ወገኖች ጋር በርካታ ግንኙነቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ተናገሩ።

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ግንኙነቶችን በመፍጠር ጦርነቱ መቋጫ እንዲያገኝ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠርና በመጨረሻም በውይይት ሰላም እንዲወርድ አዘውትረው ሲጥሩ መቆየታቸውን ዋና ፀሐፊው ተናግረዋል።

"ሁሌም ግጭቱ እንዲቆም፣ ሰብአዊ እርዳታ በሁሉም ቦታ እንዲዳረስ እንዲሁም ሰላምን የሚያመጣ ውጤታማ ድርድር እንዲደረግ ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ" ብለዋል ጉቴሬዝ።

ዋና ፀሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ይህንን ለቢቢሲ የተናገሩት በዚህ ሳምንት የምዕራብ አፍሪካ አገራት በሆኑት በሴኔጋል፣ በኒጀር እና በናይጄሪያ ጉብኝት ባደረጉበት ጊዜ ነው።

የትግራይ ክልልን በሚመራው የህወሓት ኃይሎችና በፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት መካከል አንድ ዓመት ተኩል ያስቆጠረው ጦርነት ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመትን ያስከተለ ሲሆን እስካሁን ድረስ ማብቂያ አላገኘም።

ከወራት በፊት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጦርነቱን ለማብቃትና ሰላም ለማውረድ የሚያስችል የሚታይ ጥረት እየተደረገ መሆኑ እንዳስደሰታቸው ከአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ከሆኑት ከኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ጋር ከተወያዩ በኋላ ገልጸው ነበር።

ጉቴሬዝ ከዚህ በፊት ለቢቢሲ አፍሪካ ሲናገሩ "በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን የተመለከተ ግልጽ የሆነ የሃሳብ ልዩነት" ቢኖርም ለጦርነቱ መፍትሄው ቅርብ ነው ብለው ነበር።

ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ሕብረት እና አሜሪካ በሁለቱ ወገኖች መካከል ድርድር እንዲካሄድና ለጦርነቱ ዘላቂ መፍትሔ እንዲገኝ ጥሪ ከማቅረብ አልፈው ለወራት የዘለቁ የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርጉም ተጨባጭ ውጤት ማስገኘት አልቻሉም።

አልፎ አልፎ ሪፖርት ከሚደረጉ ግጭቶች ባሻገር በሁለቱ ኃይሎች መካከል የሚደረግ ጦርነት ጋብ ያለ ሲሆን፣ ከአንድ ወር በፊት ደግሞ ወደ ትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ እንዲቻል በሚል በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የታወጀውን የተኩስ አቁም ህወሓትም መቀበሉ ይታወሳል።

የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ የቀድሞው የናይጄሪያ መሪ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ እንዲሁም የቀድሞውና የአሁኑ የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን እና ዴቪድ ሳትርፊልድ ተደጋጋሚ ጥረት እያደረጉ መሆናቸው በተለያየ ጊዜ ቢነገርም ስለደረሱበት ውጤት እስካሁን ያሉት ነገር የለም።

ከወራት በፊት የህወሓቱ መሪ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተዘዋዋሪ ውይይት እየተደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸው የነበረ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ማስተባበሉ ይታወሳል።

ሁለት ዓመት ሊሞላው ስድስት ወራት የቀሩት ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት፣ የአማራና የአፋር ክልሎችንም ያዳረሰ ሲሆን ጦርነቱ በአገሪቱ ላይ የተለያየ ጫናን አሳድሯል።