ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከቡና ጋር ተቀላቅሎ የተላከ 500 ኪሎ ግራም ኮኬይን ተያዘ
የስዊዘርላንድ ፖሊስ ቡና አምራች ወደሆነው ኔስፕሬሶ ፋብሪካ ከቡና ጋር ተቀላቅሎ የተላከ 500 ኪሎ ግራም ኮኬይን መያዙን አስታወቀ።
የፋብሪካው ሠራተኞች ቡና በሚላክበት ከረጢት መካከል ነጭ ዱቄት ከተመለከቱ በኋላ ጉዳዩን ለፖሊስ ሪፖርት አድርገዋል።
ፖሊስ በቦታው ተገኝቶ ተጨማሪ ፍተሻዎችን ካደረገ በኋላ በአምስት እቃ መላኪያ ኮንቴነሮች ውስጥ በጠቅላለው 500 ኪሎ ግራም የሚመዝን ኮኬይን አግኝቷል።
እስካሁን ባለው ምርመራ እጹ ከቡና ምርት ጋር ተቀላቅሎ የተላከው ከደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ብራዚል ነው።
እውቁ ቡና አምራች ኩባንያ ኔስፕሬሶ ክስተቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ የቡና ፍሬ በእጹ አልተበከለም ብሏል።
"ተጠቃሚዎቻችን በሙሉ ምርቶቻችን ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን" ብሏል ቡና አምራች ኩባንያው።
ይህ ኮኬይን ለገበያ ቢቀርብ ከ53 ሚሊዮን ዮሮ በላይ ሊያወጣ እንደሚችል ተገምቷል።
ፍብሪካው የሚገኝበት አካባቢ የደኅንነት ኃላፊ የሆኑት ማርክ አንድሬ፤ "የተያዘው መጠን እጅግ ትልቅ፤ የማይጠበቅ መጠን ሊባል ይችላል" ብለዋል።
ፖሊስ ይህ እጽ እንዴት ወደ ቡና አምራች ፋብሪካ ሊመጣ እንደቻለ ያለው ነገር ባይኖርም፤ ለአውሮፓ ገበያ ሊቀርብ ታስቦ የነበረ ሳይሆን አይቀርም ብሏል።