ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኤምሬትስ አየር መንገድ ወደ ሩሲያ መብረሬን እቀጥላለሁ አለ
የኤምሬትስ አየር መንገድ ኃላፊ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥት ክልከላ ካልጣለ በስተቀር አየር መንገዱ ወደ ሩሲያ የሚያደርገውን በረራ እንደሚቀጥል አስታወቁ።
"አቁሙ ከተባልን እናቆማለን ካልሆነ በየጊዜው የምናደርገው በረራችንን እንቀጥላለን" ሲሉ ኃላፊው ሰር ቲም ክላርክ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የዩክሬን ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ምዕራባውያን ሃገራት በርካታ ማዕቀቦችን ጥለዋል እንዲሁም ዋና ዋና የሚባሉ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶችም ሩሲያን ለቀው ወጥተዋል።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የኤምሬትስ አየር መንገድ ወደ ሩሲያዎቹ ሞስኮና ሴንት ፒተርስበርግ ከተሞች በረራዎችን ከሚያደርጉ ጥቂቶቹ አንዱ በመሆን ቀጥሏል።
አየር መንገዱ ይህንን አቋም እንደገና ያጤነው እንደሆነ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄም የአየር መንገዱ ኃላፊ የእሳቸው ውሳኔ ሳይሆን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥት የሚወስደው እርምጃ ነው ብለዋል፥
አየር መንገዱ መንገደኞችን ከማጓጓዝ በተጨማሪ በማዕቀቡ ዝርዝር ውስጥ ያልተካተቱ የሰብአዊ ቁሳቁሶችን የምግብና የህክምና አቅርቦቶችን ጨምሮ ሌሎች ጭነቶችን ያጓጉዛል።
ኃላፊው አክለውም የሩሲያ ህዝብ በዩክሬን ውስጥ ያለው ጦርነት አካል ላይሆን እንደሚችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
እናም በሞስኮ ውስጥ ተልእኮ ያላቸው ሌሎች ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ስራቸውን ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት እና በመውጣት መስራት መቻል አለባቸው ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
" በምናደርጋቸው በረራዎች በዋናነት ህዝብን እያገለገልን ነው፤ ምናልባትም የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ መንግሥት የሚመለከተው በዚህ መንገድ ነው" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የነዳጅ ጭማሬ ቢኖርም በረራዎችም በዚሁ መጠን መጨመራቸውን ይናገራሉ።
አየር መንገዱ የነዳጅ ጭማሬውም ጋር በተያያዘ በአውሮፕላን ታሪፎች ላይ ተጨማሪ ዋጋ ቢጥልም ይህ ሁኔታ በመንገደኞችም ላይ ሆነ በጭነት አጓጓዦች ላይ ያመጣው ለውጥ የለም ይላሉ።