ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጋዝ ክፍያ በሩብል እንዲሆን የጠየቀችው ሞስኮ የጋዝ አቅርቦት አይቋረጥም አለች
ሩሲያ ለአውሮፓ ሕብረት የምትልከውን ጋዝ እንደማታቋርጥ ብታስታውቅም አገራቱ ግን ለሚገዙት የጋዝ ምርት ክፍያቸውን በሩብል እንዲፈጽሙ መጠየቋ አከራካሪ ሆኗል።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ከአርብ ዕለት ጀምሮ የሞስኮን ጋዝ የሚገዙ የሩሲያውን መገበያያ ሩብል በመጠቀም በሩሲያ ባንኮች አማካይነት ከፍያ እንዲፈጽሙ አዘዋል።
ክሬምሊን እንዳስታወቀው ቀድሞ ክፍያ የተፈጸመባቸው ግዢዎች ይህ ሕግ እንደማይመለከታቸው እና ከያዝነው የፈረንጆቹ አዲስ ወር መጀመሪያ እስከ አጋማሽ ድረስ ወደ ገዢዎች እንደሚላኩ አስታውቋል።
የምዕራቡ ዓለም አገራት ሩሲያ ላይ የጣሉትን ማዕቀቦች ተከትሎ ነው ሩሲያ መገበያያ ገንዘቧን ለማጠናከር መሰል እርምጃዎችን ለመከተል የተገደደችው።
ክፍያዎቹ በሩብል ስለመፈጸማቸው ማረጋገጫ ካልተገኝ የጋዝ አቅርቦቱን ሩሲያ ታቋርጣለች ማለት ግን አይደለም ሲሉ የክሬምሊን ቃል አቀባዩ ዲሜትሪ ፔስኮቭ።
የአውሮፓ ሕብረት በበኩሉ ይህንን የሩሲያ ውሳኔ ተከትሎ የኃይል አቅርቦት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ክፍያ እንዴት ሊፈጸም እንደሚቻል እያነጋገር መሆኑን አስታውቋል።
የሕብረቱ የኃይል ዳይሬክተር የሆኑት ዲቴ ዩል ዮርገንሰን በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ''የአውሮፓ ሕብረት ከአባል አገራትና ወሳኝ ዘርፎች ጋር በቅርበት እየሰራ ነው። ለሩሲያ የሚፈጸሙ ክፍያዎች በምን አይነት ገንዘብ እንደሚከናወኑ መግባቢያ አማራጮችን እየፈለግን ነው'' ብለዋል።
ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ የምዕራቡ ዓለም አገራት በርካታ የሩሲያ መንግሥት ላይ፣ የሩሲያ ድርጅቶች እና ባለሃብቶች ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።
በሌላ በኩል ከአሜሪካ እና ካናዳ በተለየ መልኩ የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ጋዝ ግዢ ላይ ማዕቀብ መጣል አልቻለም።
ምክንያቱ ደግሞ 40 በመቶ የሚሆነውን የአውሮፓ ህብረት የጋዝ ፍላጎት የምታቀርበው ሩሲያ ናት።
ከዚህ በፊት በነበሩት የንግድ እንቅስቃሴዎች መሰረት የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ክፍያ የሚፈጽሙት በዩሮ እና በዶላር ነበር።
የአውሮፓ ሕብረት አባላ አገራት የሩሲያ የጋዝ አቅርቦት ቢቋረጥ ሌላ አማራጭ ማግኘት ቀላል አይሆንላቸውም። ሩሲያ በየዕለቱ ለሕብረቱ ጋዝ እየሸጠች 400 ሚሊዮን ዩሮ ትሰበስባለች።
ሩሲያ ምናልባት የጋዝ አቅርቦቷን ልታቋርጥ ትችላለች የሚል ስጋት የገባቸው የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ሁኔታውን በቅርበትና በጭንቀት እየተከታተሉት ነው።
ረቡዕ ዕለት ጀርመን እና ኦስትሪያ የተመጠነ ጋዝ ለዜጎቻቸው ማከፋፈል ጀምረዋል። የጀርመን መንግስት ተጠቃሚዎችና ድርጅቶች በተቻላቸው መጠን የጋዝ አጠቃቀማቸውን እንዲከታተሉና እንዲቀንሱ ጠይቋል። ኦስትሪያ በበኩሏ የጋዝ ገበያው ወዴት እያመራ ነው የሚለውን እየተከታተለቸውን እንደሆነ አስታውቃለች።