ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የናይጄሪያ ታጣቂዎች በባቡር ላይ ባደረሱት ጥቃት መንገደኞች ተገደሉ
በናይጄሪያ ርዕሰ መዲና አቡጃ እና ካዱና ከተማ በሚመላለስ ባቡር ላይ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ሰባት ተሳፋሪዎች መሞታቸውን የሆስፒታሉ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግሩ።
ታጣቂዎቹ ሰኞ ምሽት ሃዲዱ ላይ ፍንዳታ በማድረስ 970 ተሳፋሪዎችን አሳፍሮ የነበረውን ባቡር አስገድደው አስቁመውታል።
በመቀጠልም ታጣቂዎች ባቡሩን ከበው ተኩስ መክፈታቸውን አንድ ተሳፋሪ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ መንገደኞች ታፍነው ተወስደዋል።
ባቡሩ በሁለቱ ከተሞች መካከል አስተማማኝ ነው ተብሎ በሚታሰበው የትራንስፖርት ዘዴ ነው።
ለገንዘብ ሲሉ እገታ መፈጸም በመላ ናይጄሪያ የተለመደ ሆኗል።
ታጣቂዎች በተለያየ ቦታ በመጠበቅ ተሽከርካሪዎችን ዒላማ ስለሚያደርጉ የአቡጃ-ካዱና አውራ ጎዳና በሃገሪቱ ካሉ አደገኛ መንገዶች አንዱ ሆኗል።
ይህም መንገደኞች 150 ኪሜ የሚረዝመውን መንገድ በመተው ብዙዎች ፊታቸውን እአአ በ2016 ሥራ ወደ ጀመረው የባቡር መስመር እንዲያዞሩ ገፋፍቷቸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በሁለቱ ከተሞች መካከል ያለው የባቡር መስመር ዒላማ ሲደረግ ያሁኑ ለለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን እጅግ አሳሳቢውም አሳሳቢውም ነው ተብሏል።
ሰኞ ማምሻውን ጥቃቱ የደረሰባቸው 22 ሰዎች ካዱና በሚገኘው ወታደራዊ ሆስፒታል በህክምና ላይ ይገኛሉ።
በካዱና በሆስፒታል በጎ ፈቃደኝነት ሆና የምትሠራ አንዲት ሴት ለቢቢሲ እንደተናገረች በቦታው ከነበሩ ሰዎች እንደሰማችው ጥቃቱ "አስፈሪ" እና "አሰቃቂ" ነው።
አንድ የባቡር መስመሩ ሠራተኛ እራሱን ጨምሮ "25 ሰዎችን ወደ ጫካ" ሲወስዱ ከአጋቾቹ ሮጦ ማምለጥ እንደቻለ ተናግሯል።
ሌላኛዋ ደግሞ የተተኮሰባት "ጥይት በጉልበቷ አለፎ" በኋላም ወታደሮች እንደረሱላት ተናግራለች።
አንድ ከፍተኛ የደህንነት ምንጭ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለፁት ወታደሮች በፍጥነት ወደ ስፍራው ደርሰዋል።
"በፍጥነት በቦታው የደረሱት ወታደሮች ጥቃቱን መክተዋል። ወታደሮቹ ሲደርሱ ነው አሸባሪዎቹ የሸሹት። ባቡሩ ጥይት የማይበሳው በመሆኑ ወለሉ ላይ ተኝተው የነበሩትን ተሳፋሪዎች ከጉዳት ተከላክሏል" ብለዋል።
የናይጄሪያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን (ኤንአርሲ) በሁለቱ ከተሞች መካከል ያለውን ሥራ አቁሟል።
የካዱና ግዛት አስተዳዳሪ ጥቃቱን "የሽብር" ድርጊት ሲሉ አውግዘው ለተጎጂዎች ቤተሰቦችም መጽናናትን ተመኝተዋል።
የባቡር መስመሩ ከሰሜን ምዕራብ ግዛቶች ወደ አቡጃ እና ወደ ደቡብ አቅጣጫ ለመጓዝ ለሚፈልጉ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች አገልግሎት ይሰጣል።
የካዱና ግዛት ባለስልጣናት ሁሉም ተሳፋሪዎች የት እንዳሉ እና ማን በትክክል እንደጠፋ ለማወቅ ከኤንአርሲ ጋር ግንኙነት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
ለገንዘብ ሲሉ ግድያና አፈና የሚፈጽሙ የታጠቁ ቡድኖች በሚገኙበት በሰሜን ናይጄሪያ ወታደሩ በአውሮፕላን ጭምር ጥቃት ቢፈጸምም ጥቃት ከማድረስ አላገዳቸውም።
ባለፈው ቅዳሜ የካዱና ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥቃት ማድረሳቸው ይታወሳል።