ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኮንሶ ዞንና አሌ ወረዳ በተከሰተ ግጭት ህይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙ ተገለጸ
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ በሚገኙት የኮንሶ ዞንና አሌ ልዩ ወረዳ ከሰሞኑ በተከሰተ ግጭት የሰዎች ህይወት መጥፋቱን፣ ቤቶች መቃጠላቸውንና ንብረት መውደሙን የአካባቢው ባለስልጣናት ለቢቢሲ ተናገሩ።
መጋቢት 09/2014 ዓ.ም በተነሳውና እስከ ትናንት በስቲያ በቀጠለውም ግጭት በኮንሶ በኩል አስካሁን ቁጥሩ በትክክል ያልታወቀ የሰዎች ህይወት ማለፉን፣ በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን እንዲሁም በሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን አቶ ሠራዊት ዲባባ በኮንሶ ዞን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
"የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ ቤቶች ተቃጥለዋል፣ ንብረት ወድሟል፣ የአካል ጉዳት ተመዝግቧል። ይህ ጉዳት ደግሞ የሁላችንም ህመም ነው። እጅግ በጣም አሳዝኖናል" ብለዋል አቶ ሠራዊት።
በአሌ ወረዳ በኩልም እንዲሁ በተመሳሳይ የሰው ህይወት መጥፋትን ጨምሮ፣ የአካል ጉዳትና ከፍተኛ የንብረት ውድመት እንዳጋጠመ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የአሌ ልዩ ወረዳ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ገሚሶ ገሳቶ ያስረዳሉ።
ለግጭቱ መነሻ የሆነው በኮንሶ ዞንና አሌ ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች ባለ የኩታ ገጠም እርሻ መሬት የይገባኛል ጥያቄ እንደሆነም ሁለቱም ባለሥልጣናት ይናገራሉ።
የሰሞኑ ግጭት ከእርሻና ግጦሽ መሬት ጋር በተያያዘ የይገባኛል እንዲሁም የከብት ዝርፊያዎችና በሰዎች ላይ በደረሰ ጥቃት ግጭቱ ማገርሸቱንም ያስረዳሉ።
ከሰሞኑም በኮንሶ በኩል የኮልሜ ክላስተር እንዲሁም በአሌ በኩል ደግሞ ገዋዳ ክላስተር የሚባሉ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ በሚገኙ አርሶ አደሮች መካከል የተፈጠረው ግጭት መባባሱን የጠቆሙት አቶ ገሚሶ "የግጭቱ መነሻ በግለሰቦች መካከል የነበረ ቢሆንም ወደ ማኅበረሰቡ መስፋፋቱን" አመልክተዋል።
በዋነኝነት ግን የችግሩ መነሻ የወሰን ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊዎቹ፣ በአንድ ወቅት ሁለቱ ሕዝቦች በአንድ መዋቅር፣ የሰገን አካባቢ ሕዝቦች በሚባል ዞን ስር አብረው ይኖሩ በነበሩበት ወቅት የተላለፉ የወሰን ውሳኔዎች ናቸው ይላሉ።
የዞኑ ካቢኔም ይህንን ችግር ገምግሞ የጋራ ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ፣ ኮንሶ ዞን ሲሆን አሌ ደግሞ በልዩ ወረዳነት እንዲቀጥል ተደርጓል።
ከወሰን የእርሻ መሬት ይገባኛል ጋር ተያይዞ በሚነሳው ጥያቄ በ2003 ዓ.ም እንዲሁም በ2006 ዓ.ም ተመሳሳይ ግጭቶች ተከስተው በእርቅ መቋጨት መቻላቸውን አቶ ገሚሶ ያስረዳሉ።
ከሁለት ዓመት በፊት በ2012 የተከሰተውም ግጭት አምና ታኅሣሥ አካባቢ በእርቅ እልባት ማግኘት መቻሉንም አስታውሰዋል።
እርቁንም ተከትሎ በዘላቂነት የወሰን ጉዳይና በተለይም በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች በጋራ መኖር የሚችሉበት ሁኔታን ለማመቻቸት የክልሉ መንግሥት የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁሞ ሥራ እየተሰራም እንደነበር አቶ ገሚሶ ያወሳሉ።
ወሰኑን በተመለከተ በሁለቱም መዋቅሮች ከሚገኙ የአገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎችና የሃይማኖት አባቶች የተውጣጣ ኮሚቴ ተደራጅቶም በዘላቂነት ለመፍታት እየሰሩ እንደነበር አስረድተዋል።
በዚህም የሁለቱም ሕዝቦች "ሰላም ዳግም እንዲያብብና እርቀ ሰላም ጉባኤዎች ተደርገው የሕዝቡ ሰላም እንዲመለስ ተደርጎ ነበር" ይላሉ አቶ ሠራዊት።
በዚህ ሁኔታ ላይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሞከረ ባለበት ወቅት አሁን የተከሰተው ጉዳት ያስከተለ ግጭት ያልተጠበቀ እንደሆነ አቶ ሠራዊት ተናግረዋል።
አቶ ገሚሶ ከሆነ ሰሞኑን ለተነሳው ግጭት፣ በኮንሶም በአሌም "ሰላሙን የማይፈልጉ" ያሏቸው ግለሰቦችን ወንጅለዋል።
"የግጭት ነጋዴ የሆኑ ግለሰቦች በሁለቱም መዋቅር አልጠፉም። በተደጋጋሚ ከብቶችን የመዝረፍ፣ በተደጋጋሚ ትንኮሳ የመፈጸም፣ በሰዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ታይቷል፣ እነዚህም ሁኔታዎች ሲደገጋሙ ግጭቱ እንዲያገረሽ አድርጓል" ብለዋል።
ካለፈው ሳምንት አርብ በፊት በረሃዎ በተባለ አካባቢ የታጠቁ ግለሰቦች ከደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ጋር ተኩስ ልውውጥ አድርገው ጉዳት የደረሰባቸው የልዩ ኃይል አባላት እንዳሉና ቁጥራቸውንና ጉዳታቸውን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው አመልክተዋል።
ከአርብ ዕለት ጀምሮም ዲመያ የሚባል አካባቢ ግጭቱ እንደገና አገርሽቶ ለሦስት ቀናት ያህልም የተኩስ ልውውጥ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም ህይወት መጥፋትን ጨምሮ የተጎዱ ሰዎችና ከፍተኛ የንብረት ውድመት እንዳጋጠመ መረጃ እንደደረሳቸው አቶ ገሚሶ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ግጭቱ እስከ ትናንት በስቲያ እሁድ ድረስ የቀጠለ ሲሆን፣ በአሌና በኮንሶ ያሉ አስተዳደሮችና የፀጥታ መዋቅሮች እንዲሁም የክልሉ ልዩ ኃይል አመራሮች በተገኙበት የጋራ ውይይት ተደርጎ መቋጫ እንዲገኝለት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ሁለቱም ባለሥልጣናት ለቢበሲ ገልጸዋል።
በዚህም ግጭት ማቆም፣ በአካባቢው ላለው እንቅስቃሴ ጥበቃ በማድረግ ጥፋት የሚያስከትለው ችግር እንዲቆምና የአካባቢው ሚሊሻና የሁለቱ መዋቅሮች ፖሊስ አባላት በስብጥር ተደራጅተው በቡድን የአካባቢውን ደኅንነትና እንቅስቃሴ እንዲጠብቁ ይደረጋል ተብሏል።
በተጨማሪም በአዋሳኝ አካባቢዎቹ በኮንሶም በአሌም የሕዝብ ውይይቶች እንዲደረጉና እነዚህንም ውይይቶች ዋና አስተዳደሪው እንዲመሩት በማድረግ በአካባቢው ማኅበረሰቦች ዘንድ ዘላቂ ሰላም እንዲወርድ ለማድረግ ተወስኗል።
በተጨማሪም በክልሉ ቴክኒክ ኮሚቴ የተጀመሩ የዘላቂ መፍትሄ ሥራዎች ይህ ግጭት ሲያገረሽ የቆሙበት ሁኔታ በመኖሩ እንደገና እንዲቀጥሉም ተወያይተዋል።
ካለፈው ሳምንት ማብቂያ አንስቶ ለቀናት ሲካሄድ የነበረው ግጭት ሰኞ ዕለት በተወሰነ መልኩ እንደረገበና የተኩስ ድምፅም እንዳልተሰማ አቶ ገሚሶ ገልጸዋል።
የኮንሶ ሕዝብና የአሌ ልዩ ወረዳ ቤተሰባዊና በተመሳሳይ ጎሳ ሥርዓት ስር ይኖሩ ነበር የሚሉት አቶ ሠራዊት፣ ይህ ችግር በክልሉ ቡድን አጥኚ በኩል እልባት እንዲያገኝም ጠይቀዋል።
ከዚህ ቀደም በአካባቢው በተለያዩ ጊዜያት ተደጋጋሚ ግጭቶች እያጋጠሙ በሰውና በንብረት ላይ ከሚደርሰው ጉዳት በተጨማሪ፣ በርካታ የአካባቢውን ነዋሪዎች ለመፈናቀል መዳረጋቸው ይታወሳል።