የጉጂ አባ ገዳ መኖሪያ ቤታቸው ላይ 'ኦነግ ሸኔ' ጥቃት መፈጸሙን ተናገሩ

የኦሮሞ አባ ገዳዎች ሕብረት ሰብሳቢ እና የጉጂ አባ ገዳ የሆኑት ጂሎ ማንዶ ታጣቂዎች በመኖሪያ ቤታቸው ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።

አባ ገዳ ጂሎ ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ዕለት መጋቢት 14/2014 ዓ.ም. ከእኩለ ሌሊት በኋላ በቤታቸው ላይ ለተፈጸመው ጥቃት እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራውን እና መንግሥት ሸኔ የሚለውን ታጣቂ ቡድን ተጠያቂ አድርገዋል።

የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ ግን ታጣቂዎቻቸው 'የተባለውን ጥቃት አልፈጸሙም' ሲሉ አስተባብለዋል።

አባ ገዳው ጥቃት በተፈጸመበት ዕለት በመኖሪያ ቤታቸው ባለመኖራቸው ከጥቃቱ መትረፋቸውንና በንብረት ላይ ከደረሰው ውጪ በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱን ገልጸዋል።

"በቁጥር ስንት ሆነው እንደመጡ ባላውቅም በአራት ሞተር ሳይክሎች መጥተው ቤቱ ላይ ተኩስ ከፈቱ። በርካታ ጥይት ተኩሰው ቤት ሰባብረው፣ ቤት ውስጥ የነበረ አንድ ኩንታል ቡና በትነው ሄዱ እንጂ ሰው እና ከብት ምንም አልሆነም" በማለት የነበረውን ሁኔታ አባ ገዳ ጂሎ ያስረዳሉ።

አባ ገዳው ታጣዊዎች ትጥቅ ፈትተው የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ጥሪ ማስተላለፋቸው የጥቃቱ ዒላማ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ያምናሉ።

"እነርሱ መጀመሪያም ቂም ይዘውብኝ ነበር። እየደወሉ፤ 'የኦሮሞ ነጻነት ጦር በሰላም ግቡ እያልክ የምትቀሰቅሰው አንተ ነህ' ሲሉኝ ቆይተዋል" በማለት አባ ገዳው ይናገራሉ።

"እየደወሉ '600 የሚሆን ሠራዊት አስገብተህ (ትጥቅ አስፈትተህ) መሳሪያቸውን ወርሰሃል፤ ያን መሳሪያ እስክታመጣ በሕይወትህ ፍረድ' ይሉኛል" ሲሉ ጂሎ ማንዶ ከታጣቂዎቹ ይደርስባቸው ስለነበረው ዛቻ ያስረዳሉ።

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ቃል አቀባይ የሆነው ኦዳ ተርቢ፤ የኦሮሞ ነጻነት ጦር አባ ገዳዎችን እና የገዳ ሥርዓትን እንደሚያከብር ገልጸው፤ "በከረዩ አባ ገዳዎች ላይ የተፈጸመውን እና የመንግሥት (የዐቢይ) ጦር ለሥርዓቱ ያለውን ንቀት ከግምት በማስገባት ይህ የተፈጸመው በእነርሱ (በመንግሥት ጦር) ሊሆን ይችላል" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የጉጂ እና የቦረና አባ ገዳዎች 'ኦነግ ሸኔ' የኦሮሞ ጠላት ነው በማለት ማወጃቸው ይታወሳል። ታጣቂዎች ትጥቅ እንዲፈቱም ጥሪ አስተላልፈዋል።

አባ ገዳ ጂሎ እንደሚሉት በሚደርሱባቸው የግድያ ዛቻዎች ምክንያት ለሕይወታቸው እንደሚሰጉ እና ባለፉት ሦስት ዓመታት ከመኖሪያ ቀያቸው ወጥተው ከተማ ውስጥ "ቤት ተከራይቼ ነው እየኖርኩ ያለሁት" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሚደርሷቸው ዛቻዎች ምክንያት ገጠር ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እንደማይሄዱ፣ በዚህም ሳቢያ ገጠር በተከናወነ የልጃቸው ሠርግ ላይ እንኳ መገኘት አለመቻላቸውን ይገልጻሉ።

"ጉጂ ሰላም ርቋታል" በማለት በአካባቢው የሰላም እጦት መኖሩን የሚናገሩት አባ ገዳው፣ ታጣቂዎቹ በርካታ የምዕራብ ጉጂ ወረዳዎችን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ ይናገራሉ።

እንደ አባ ገዳ ጂሎ ከሆነ ባለፉት ሦስት ዓመታት በርካታ ንጹሃን የአካባቢው ነዋሪዎች በታጣቂዎቹ ተገድለዋል።

"የታጣቂዎቹ ካምፕ ሄጄ ሰላም አውርዱ ብዬ ለምኛለሁ፤ 'በአፈሙዝ እንጂ አንታረቅም' አሉ። እንደ እኔ ስለ ሰላም የሰበከ የለም። መንግሥት እና እነሱን (ታጣቂዎቹን) ለማስታረቅ ፍላጎት ስላለኝ ጠሉኝ እንጂ እኔ ለየትኛውም አካል አልወግንም" በማለት የተለየ ድጋፍ እንደሌላቸው አባ ገዳው ይናገራሉ።

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራውና መንግሥት ሸኔ የሚለው ታጣቂ ቡድን ከጥቂት ዓመታት በፊት ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ተለይቶ የወጣ ታጣቂ ቡድን ነው።

በተለይ በምዕራብና ደቡብ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው ይህ ኃይል በተለያዩ ጊዜያት በሰላማዊ ሰዎች እና በአካባቢ ባለሥልጣናት ላይ ከሚፈጸሙ ግድያዎች ጋር ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል።

ከህወሓት ጋር አጋር በመሆን የኢትዮጵያ መንግሥትን ለመጣል መስማማቱን ይፋ ያደረገው ታጣቂ ቡድኑ በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት መፈረጁ ይታወሳል።