ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሜክሲኮ ውስጥ በእግር ኳስ ጨዋታ መሃል በተነሳ ግጭት 26 ሰዎች ተጎዱ
ሜክሲኮ ውስጥ በአንድ የእግር ኳስ ጨዋታ መሃል በተነሳ ግጭት ቢያንስ 26 ሰዎች ጉዳት ደረሰባቸው።
ሊጋ ኤምኤክስ በተሰኘው የሜክሲኮ ከፍተኛው የእግር ኳስ ሊግ ቡድኖች በሆኑት ኩዌርታሮ እና አትላስ መካከል የነበረው ፍልሚያ በ63ኛው ደቂቃ ተቋርጧል።
ላ ኮሬጊዶራ በተባለው ስታድዬም ብጥብጥ ሲነሳ ተጨዋቾች ደጋፊዎችን ለማረጋጋት ቢሞክሩም ሁኔታው ሲብስ ግን ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ ተገደዋል።
ሶስት ሰዎች ክፉኛ ሲጎዱ በጠቅላላው 26 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና እርዳታ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
"ምንም እንኳ ሰዎች ባይሞቱም ይህ ክስሰተት አሳዛኝ አይደለም ማለት አንችልም" ሲሉ የኩዌርታሮ ግዛት ሃገረ ገዥ ማውሪሲዮ ኩሪ ተናግረዋል።
ሃገረ ገዥው አክለው ጉዳት ከደረሰባቸው 26 ሰዎች መካከል ሶስቱ ሕክምና አግኝተው ሲወጡ ሶስቱ ደግሞ አደገኛ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።
ከሜዳቸው ውጭ እየተጫወቱ የነበሩት አትላሶች ጨዋታውን አንድ ለባዶ እየመሩ ሳለ ነው ግርግሩ የተነሳው።
የሊጋ ኤምኤክስ ፕሬዝደንት ሚኬል አሪዮላ፤ ለጉዳቱ ሃዘኔታ ለማሳየት ሲባል ሌሎች ጨዋታዎች እንደሚቋረጡ ገልጠዋል።
"በስታድዬም ውስጥ ግርግር ሲነሳ ሁኔታውን መቆጣጠር ያልቻሉ የፀጥታ አካላት ቅጣት ይጣልባቸዋል" ሲሉም አክለዋል።
የዓለም እግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ ክስተቱን "ተቀባይነት የሌለውና የማንታገሰው" ብሎታል።
ፊፋ በፅሑፍ ባወጣው መግለጫ አክሎ "የአካባቢው ባለሥልጣናት ብጥብጡን ያስነሱ ሰዎችን ለሕግ እንዲያቀርቡ" ጠይቋል።