በአፍሪካ የልጆች ፎርሙላ ወተት በአስጊ መንገድ እየተዋወቀ እንደሆነ ጥናት አመለከተ

ናይጄሪያ ውስጥ ከሚወልዱ እናቶች መካከል ግማሾቹ፣ በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ እናቶች አንድ አምስተኛ የሚሆኑት እንዲሁም በሞሮኮ ደግሞ ከአምስት እናቶች ሁለቱ ለልጆቻቸው የሕፃናት ወተት ፎርሙላዎችን እንዲጠቀሙ በጤና ባለሙያዎች እንደሚነገራቸው የዓለም ጤና ድርጅት እና የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) በጋራ በሠሩት ጥናት አረጋግጠዋል።

''ይህ ሪፖርት የሕፃናት ወተት ፎርሙላዎችን ማስተዋወቅ ተቀባይነት በሌለው መልኩ የተስፋፋና አሳሳች እንዲሁም በተጠናከረ መንገድ የሚደረግ እንደሆነ አሳይቷል'' ብለዋል የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም።

ናይጄሪያ እና ሞሮኮ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች እንደተናገሩት የሕፃናት ወተት ከሚያመርቱና ከሚሸጡ ድርጅቶች ጋር መሥራት በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ባሉ የጤና ማእከላት ውስጥ በጣም የተለመደ ነገር ነው።

ጥናቱ የተካሄደው 8500 ቤተሰቦችና እናቶችን በማካተት ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በመላው ዓለም እንደ ባንግላዲሽ፣ ቻይና፣ ሜክሲኮ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ቬትናም ባሉ አገራት የሚገኙ 300 የጤና ባለሙያዎቸንም ተሳታፊ አድርጓል።

''ጠንካራ የሆኑ መመሪያዎችና ፖሊሲዎች ያስፈልጉናል። እናቶች ተገቢ ባልሆነ መንገድ የሚቀርብላቸውን የሕፃናት ወተት እንዳይጠቀሙና ጡት ማጥባትን ለማበረታታት አዋጪ ኢንቨስትመንቶች ያስፈልጉናል። ሴቶች ልጆቻቸውን ስለማሳደግና ቤተሰባቸውን ስለመደገፍ በቂ እውቀት ሊኖራቸውና መረጃው ሊቀርብላቸው ይገባል'' ሲሉ አሳስበዋል ዶ/ር ቴድሮስ።

የእናት ጡት ወተት አዲስ ለተወለዱ ሕፃናት አቻ የማይገኝለት ምግብ ነው።

ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ንጹህ እንዲሁም በርካታ ሕፃናት ላይ የሚከሰቱ በሽታዎችን መከላከል የሚያስችሉ አንቲቦዲዎች በውስጡ የያዘ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው እናቶች አዲስ የተወለዱ ልጆቻቸውን ቢያንስ ለስድስት ወራት ማጥባት ያለባቸው ሲሆን ይህም የሕፃናቱን ደኅንነትና በሕይወት የመቆየት ዕድል በእጅጉ ከፍ ያደርገዋል።

የእናታቸውን ጡት ጠብተው ያደጉ ሕፃናት የአእምሮ ብቃት መመዘኛ ፈተናዎች ላይ የተሻለ ውጤት ነው የሚያስመዘግቡት።

ከልክ ያለፈ ውፍረት የማጋጠም ዕድሉም ቢሆን ዝቅተኛ ሲሆን ካደጉ በኋላ በስኳር በሽታ የመጠቃት ዕድላቸውም የወረደ ነው።

በሌላ በኩል ልጆቻቸውን ጡት የሚያጠቡ እናቶች በጡት እንዲሁም በኦቫሪያን ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው የቀነሰ ነው።