ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያዊው የእግር ኳስ ኮከብ አቡበከር ከደቡብ አፍሪካ ክለብ ጋር ከስምምነት መድረሱ ተነገረ
ወጣቱ ኢትዮጵያዊ የእግር ኳስ ኮከብ አቡበከር ናስር ለደቡብ አፍሪካው ክለብ ለመጫወት ከስምምነት መድረሱ ተነገረ።
ያለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ኮከብ ግብ አግቢ የሆነው የኢትዮጵያ ቡና አጥቂው አቡበካር ናስር ከስምምነት የደረሰው ከደቡብ አፍሪካው ኃያል ቡድን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር ነው።
አቡበካር በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ለታዋቂው ኢትዮጵያ ቡና ቡድን ከመጫወቱ ባሻገር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ካሜሩን እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በሦስት ጨዋታዎች ተሰልፏል።
የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ፕሬዝደንት የሆኑት ፈቃደ ማሞ ትናንት ምሽት በአንድ ዝግጅት ላይ አቡበከር 'ብራዚላውያኑ' በሚል ቅጽል ስያሜ ወደ ሚታወቁት ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ክለብ ዝውውር ያደርጋል የተባለውን ዜና አረጋግጠዋል።
አቡበካር ወደ ደቡብ አፍሪካው እግር ኳስ ክለብ በምን ያህል ክፍያ እንደሚያቀና አስካሁን የተባለ ነገር የለም።
የክለቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ ገዛኸኝ ወልዴ ተጫዋቹ የተዘዋወረበትን የገንዘብ መጠን ይፋ ባያደርጉም ክፍያው ከፍተኛ እንደሆነ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ፕሪሚዬር ሊግን እየመራ የሚገኘው ኃያሉ ክለብ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ስለአቡበካር ዝውውርና ሌሎች ጉዳዩን የሚመለከት ዝርዝር መረጃ አስካሁን አላወጣም።
'ብራዚላዊያኑ' አቡበከርን እስከውድድር ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ለቡና በውሰት መልሰው ሊሰጡት እንደሚችሉም ተዘግቧል።
የ21 ዓመቱ ወጣት እግር ኳስ ተጫዋች አቡበከር ናስር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ጨዋታ መሰናበቱን ተከትሎ ከደቡብ አፍሪካው ቡድን ጋር የሙከራ ጊዜ ማሳለፉ ይታወሳል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ጎል የተሰኘው ታዋቂ የእግር ኳስ ድረ-ገፅ ሌላኛው የደቡብ አፍሪካ ቡድን ካይዘር ቺፍስ አቡባካርን ለማስፈረም እንደሚፈልግ አስነብቦ ነበር።
ከዚህ በፊት ጌታነህ ከበደና ፍቅሩ ተፈራ ለደቡብ አፍሪካ ክለቦች መጫወታቸው አይዘነጋም።