በሳዑዲ አረቢያ ባሉ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ላይ የሚመክር የልዑካን ቡድን በሪያድ

በገንዘብ ሚኒስትር አሕመዴ ሽዴ የሚመራ የልዑክ ቡድን በሳዑዲ አረቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያን አያያዝ ሁኔታ ላይ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር ሪያድ እንደሚገኝ በሳዑዲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።

ይህ የልዑክ ቡድን ሳዑዲ አረቢያ መግባቱ የተነገረው በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን አስከፊ በሆነ ሁኔታ በሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ እየማቀቁ እንደሆነ በስፋት እየተዘገበ ባለበት ወቅት ነው።

የልዑክ ቡድኑ በኢትዮጵያውያን አያያዝ ሁኔታ ላይ ከመምከር በተጨማሪ፤ በሁለቱ አገራት የጋራ ጉዳዮች እና በሰሜን አገሪቱ ስላለው ጦርነት ገለጻ ያደርጋል ተብሏል።

ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንደሚሉት የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከአገሪቱ ንጉሥና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ረቡዕ ጥር 18/2914 ሪያድ የገባው የኢትዮጵያውያኑ ልዑካን ቡድን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የተለያዩ ከሃይማኖት ተወካዮችና ዲፕሎማቶች የያዘ ሲሆን አባቶች የተካተቱበት ነው።

ከእነዚህም መካከል የገንዘብ ሚኒስተት አቶ አሕመድ ሺዴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትረ ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኢድሪስ፣ ቄስ ታጋይ ታደለ፣ በሳዑዲ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ሌንጮ ባቲና ሌሎችም እንዳሉበት ታውቋል።

በነዳጅ ምርት ወደ የለጸገችው ሳዑዲ አረቢያ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሰርቶ ለመቀየር መዳረሻ ከሚያደርጓቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መካከል አንዷ ነች።

ይሁን እንጂ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በተለያየ የወቅት በአገሪቱ የሥራ እና የመኖሪያ ፍቃድ የላቸውም የሚላቸውን ኢትዮጵያውያን እጅግ አስቸጋሪ በሆኑና በጠባብ እስር ቤት እንደሚቆይዋቸው ቢቢሲ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።

እስረኞቹ በቂ ምግብ እና የሕምክና አገልግሎት ማግኘት በማይችሉበት ሁኔታ በህይወት አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ እንደሚያዙ ይናገራሉ።

ከቀናት በፊትም ቢቢሲ የደረሰው ተንቀሳቃሽ ምስል ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው። በዚህ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ በጠባብ ቦታ ላይ ታስረው የሚገኙ ዜጎች ልብሳቸው አልቆ፣ ጥቁር ፌስታል ለብሰው እና ተጎሳቁለው ይታያሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ሁኔታ የሚገኙ እና ወደ አገራቸው የመመለስ ፍላጎት ያላቸው ዜጎች ከሳዑ ሲያስወጣ ቆይቷል። ከዚህ በተጨማሪም የእስኞች አያያዝ ሁኔታን ለማስተካከል የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር በመነጋገር ሁኔታዎችን ለማሻሻል ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።

ነዋሪነታቸው በሳዑዲ አረቢያ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ግን በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ እየደረሰባቸው ያለውን እንደግልትና ሰቆቃ ለመቀነስ የኢትዮጵያ መንግሥት በቂ ጥረት አላደረገም ሲሉ ያማርራሉ።

ከኢትዮጵያውያን አስረኞች መካከል አንዱ የሆነው መሐመድ ለቢበሲ እንደተናገረው በተለያዩ የሳዑዲ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከመንግሥታቸው ምላሽ ይጠበቃሉ ይላል።

መሐመድ "የዚህ አገርን መንግሥት መውቀስ አንችልም። መውቀስም ካለብን የኢትዮጵያን መንግሥት ነው። እንዲተባበሩን መጠየቅ ካለብንም የአገራችንን መንግሥት ስለሆነ ነው" ይላል።

"የታሰሩባቸው ክፍሎች የተጨናነቁ ናቸው። አንድ ክፍል ውስጥ በብዛት ስለሚታሰሩ በሙቀት እና በሌሎችም ነገሮች ህይወት እስከ ማጣት ድረስ ችግር እየደረሰባቸው ነው" ሲል ያክላል።

በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዳሉት ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው የመመለሱ ሂደት አለመቆሙና የተወሰነ መቀዛቀዝ እንደነበር ጠቅሰው፤ እንደ ከዚህ በፊቱ በአስቸጋሪ ህይወት ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ ነው ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

በቅርቡም በሳዑዲ አረቢያ በችግር ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው የመመለሱ ዘመቻ መልሶ እንደሚጀመር ተናግረዋል።