ፖላንድ ውስጥ የናዚ ምልክት ያሳየችው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንድ ኔዘርላንዳዊት ጎብኚ ፖላንድ ውስጥ በቀድሞ የኦሽዊትዝ ቢርኬናው የግድያ ካምፕ የናዚን የሰላምታ ምልክት በማሳየቷ በቁጥጥር ሥር መዋሏ ተሰምቷል።
የ29 ዓመቷ ቱሪስት ይህንን ምልክት ያሳየችው አርቤይት ማኽት ፍሬይ ከተሰኘው የቱሪስት ሥፍራ ነው።
ስሟ ያልተጠቀሰው ግለሰብ የናዚን ፕሮፖጋንዳ በማራመድ የተከሰሰች ሲሆን አቃቤ ሕግ ያቀረበውን የቅጣት ሐሳብም ተቀብላለች ተብሏል።
ፒኤፒ የተሰኘው የፖላንድ የዜና ወኪል እንደዘገበው ጎብኚዋ ድርጊቱን የፈጸምኩት እንደ ቀልድ ነው ብላለች።
በወቅቱ በባለቤቷ አጋዥነት ከቱሪስት መገኛው ሥፍራ ፎቶ ስትነሳ ነበር ተብሏል።
ፖላንድ ውስጥ የውጭ አገር ዜጎች የናዚን የሰላምታ ምልክት በማሳየታቸው በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ፖላንድ ውስጥ ይህንን ድርጊት ሲፈጽም የተገኘ ሰው እስከ ሁለት ዓመት እስር ሊጠብቀው ይችላል።
በፈረንጆቹ 2013 ሁለት ቱርካዊ ተማሪዎች ኦሽዊትዝ ውስጥ የናዚ ሰላምታ ምልክት በማሳየታቸው እያንዳንዳቸው ስድስት ዓመት እስር መቅመሳቸው አይዘነጋም።
ተማሪዎች ለ3 ዓመታት ወደ ፓላንድ ብቅ እንዳይሉም ተፈርዶባቸው ነበር።
ናዚ ጀመርን ይህንን የግድያ ካምፕ በፈረንጆቹ 1939 በሁለተኛው ዓለም ጦርነት መባቻ የገነባው ፓላንድን በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ ነው።
በአራት ዓመት ከግማሽ ብቻ ናዚ ጀርመን ቢያንስ 1.1 ሚሊዮን ሰዎችን ኦሽዊትዝ ውስጥ የገደለ ሲሆን ከነዚ መካከል አንድ ሚሊዮን ያህሉ አይሁዶች ነበሩ።
ወደዚህ ካምፕ የሚመጡ ሞት የሚጠብቃቸው ሰዎች በረሃብ፣ በጋዝ፣ ለሞት በሚዳርግ ሥራ እንዲሁም በሕክምና ሙከራዎች ተገድለዋል።
ሆሎኮስት በተሰኘው የናዚ አይሁዶችን የማጥፋት ዘመቻ ስድስት ሚሊዮን አይሁዶች ተገድለዋል።
ይህንን ካምፕን በ1945 ነፃ ያወጡት የሶቪዬት ሕብረት ወታደሮች ነበሩ።












