ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽነርነት የሚሰየሙ ዕጩዎችን የመጠቆሚያ ጊዜ ተራዘመ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ውስጥ የሚካተቱ ዕጩ ኮሚሸነሮች የጥቆማ ጊዜ መራዘሙን አስታወቀ።
ምክር ቤቱ 'ኮሚሽኑ ከሚኖረው ከፍተኛ አገራዊ ኃላፊነት አንፃር' በተለያዩ አካላት ጥያቄ መቅረቡን ተከትሎ ተጨማሪ ዕጩዎችን ሕዝቡ እንዲጠቁም የዕጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማ እስከ ጥር 13/2014 ዓ.ም ድረስ ተራዝሟል ብሏል።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች የመጠቆሚያ ጊዜ እንዲራዘም እንዲሁም የመጨረሻዎቹ ዕጩ ኮሚሽነሮች ከተጠቆሙት ሰዎች መካከል ተለይተው የሚቀርቡበት መመዘኛ ግልጽነት እንዲኖረው ጥያቄ ሲቀርብ ነበር።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ያፀደቀው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚያመቻቸው የምክክር ሒደትን ሁሉን አካታች፣ ተዓማኒ እና ግልጽ መሆኑን ለመከታተል እየተዘጋጁ እንደሆነ ያስታወቁት 11 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ናቸው ከላይ የተጠቀሱትን ጥያቄዎች ያቀረቡት።
ለአገሪቱ አስርት ዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ሁሉን አካታች በሆነ መልኩ ለመፍታትና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያግዛል በሚል ለተቋቋመው አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኮሚሽነሮች ጥቆማ የተቀመጠው ጊዜ ታኅሣሥ 26/2014 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን የመጠቆሚያ ጊዜው ተራዝሞ ጥር 13/2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል።
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አዋጅ የኮሚሽነሮች ጥቆማ ከሕዝብ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶችና ከሲቪል ማኅበራት እንደሚሆን የደነገገ ሲሆን ይህም ሊደነቅ እንደሚገባው የጠቆመው መግለጫ የተሰጠው ጊዜ ግን አጭር ነው ብለው ነበር።
ለጊዜው ማጠር የጠቀሷቸው ምክንያቶች ከመረጃው ተደራሽነት፣ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ካለው የመገናኛ ዘዴዎች ውሱንነት፣ ብሎም ለኮሚሽነርነት ብቁ የሆኑ ሰዎችን ለማሰብ ከሚወስደው ጊዜ አንፃር በቂ ጥቆማዎች እንዳይኖሩ እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት እንደፈፈጠረባቸው አስፍረዋል።
በተጨማሪም በሕዝብ ከተጠቆሙ ኮሚሽነሮች መካከል የመጨረሻ 14ቱ ዕጩዎች በአፈ ጉባዔው ተለይተው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርቡ የተገለጸ ሲሆን፣ ዕጩዎቹ ተለይተው የሚቀርቡበትን መመዘኛን በተመለከተ የአሠራር ግልጽነት አለመኖሩን ማየታቸውን ድርጅቶቹ አስፍረዋል።
በሕዝብ የተጠቆሙት ዕጩዎች በምን መመዘኛ እንደተመረጡ ለብዙኃን ግልጽ ማድረግ የሚቻልበትን አሠራር መመሥረት ለኮሚሽኑ ተዓማኒነት ጉልህ ሚና አለው ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።
ድርጅቶቹ ባወጡት መግለጫ አገራዊ ምክክሩ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ሁሉን አካታች በሆነ መልኩ ለመፍታት ሂደቱ ግልፅ መሆን በአብዛኛው ዘንድ ለሚኖረው ተዓማኒነት እና ተቀባይነት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
በዚህም አገራዊ ምክክሩን የሚያመቻቸው ኮሚሽን ተዓማኒነቱ ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አመልክተዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የኮሚሽነሮች የመጠቆሚያ ጊዜ እንዲራዘምና የመጨረሻዎቹ ዕጩ ኮሚሽነሮች ከተጠቆሙት ሰዎች መሐከል ተለይተው የሚቀርቡበት መመዘኛ ግልጽነት እንዲኖረው ጠይቀዋል።
ጥያቄውን ያቀረቡት ድርጅቶች የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ሕብረት፣ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል፣ ኢስት አፍሪካን ኢኒሺዬትቭ ፎር ቼንጅ፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ አርታኢያን ማኅበር፣ ሴታዊት ንቅናቄ፣ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ፋውንዴሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ናቸው።