አሜሪካ የኢትዮጵያ ጦርነት እንዲቋጭ ጠንካራ ዲፕሎማሲ እየተከተልኩ ነው አለች

አሜሪካ አስራ አራተኛ ወራቱን ያስቆጠረውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቋጨት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፣ መጠነ ሰፊ ግፎችንና ሰቆቃዎችን ለማስቆም መፍትሔ እንደሆነ ተናገረች።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ ቃለ አቀባይ ኔድ ፕራይስ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ አገራቸው ጦርነቱ በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ጠንካራ ዲፕሎማሲ እየተከተለች እንደሆነ አስረድተዋል።

ከሰሞኑ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጦርነቱ በድርድር የሚቋጭበትን መንገድ አስመልክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በስልክ የተነጋገሩ ሲሆን ኔድ ፕራይስ ይህ የስልክ ወይይት የዲፕሎማሲው አካል ነው ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋባዥነት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት ተሰናባቹ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን እንዲሁም እሳቸውን የሚተኩት ዴቪድ ሳተርፊልድ ከቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ለጦርነቱ መቋጫ ለማበጀት በቅርበት እየሰሩ ነው ብለዋል።

ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ጥር 3/2014 ወደ ትግራይ መዲና መቀለ ሄደው ከአመራሮቹ ጋር መክረው የተመለሱ ሲሆን ውይይታቸውም ጥሩ እንደነበር የህወሓት ቃለ አቀባይ ተናግረዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ለተከሰተው ቀውስ መፍትሄ ለማምጣትም አሜሪካ ካሉ የቀጣናው መሪዎች፣ ከአፍሪካ ሕብረት ጋር ተቀራርባ እየሰራች ስለመሆኑም ኔድ ፕራይስ አስረድተዋል።

"አሁን ያለው ሁኔታ ለሁለቱም ወገኖች መሻሻሎች መኖራቸውን እንዲያሳዩ ይረዳቸዋል። ግጭቱን በማቆም ወደ ድርድር ጠረጴዛው ሊመጡ ይችላሉ በዚህም የሁሉም ግብ የሆነው ጦርነት እንዲቋጭ ይረዳል" ብለዋል።

በያዝነው ሳምንት ሰኞ በትግራይ ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት ቢያንስ 17 ሰዎች መገደላቸውንና አብዛኛዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰው ይህም ጥቃት የተፈጸመው ፕሬዚዳንት ባይደን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአየር ጥቃቱ እንዲቆም ካሳሰቡበት ዕለት ጋር ከመገጣጠሙ ጋር ተያይዞ ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች ተነስቷል።

በስልክ ንግግራቸው ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአየር ጥቃቱን ለማቆም ቃል ገብተዋል ወይ? የአየር ጥቃቱ መቆሙን ለማረጋገጥ አሜሪካስ ምን ታደርጋለች የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

ኔድ ፕራይስ ሲመልሱ በነበረው የመሪዎቹ ስልክ ንግግር ፕሬዚዳንት ባይደን በቅርቡ የተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች በሲቪል ዜጎች ላይ ስላደረሰው ሞት እንዲሁም ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ያላቸውን ስጋት አንስተውላቸዋል ብለዋል።

ከዚህ ቀደምም እንዳደረጉት አገራቸው የጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ ሁሉም ወገኖች ላይ የፈጸሟቸውን ጥሰቶች በተመለከተ በተደጋጋሚ ከአመራሮቹ ጋር እንዲሁም በመግለጫዎች ላይ ከማንሳት ወደ ኋላ አትልም ብለዋል።

አገራቸው ተጠያቂነት ሊኖር እንደሚገባ እንደምታምን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙ ጥሰቶችን የሚያጣራ የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብት ጉባኤ ነፃናና ገለልተኛ የሆነ ኮሚሽን እንዲቋቋም የተወሰደውን እርምጃ መደገፏ አንዱ ማሳያ ነው በማለት የአገራቸውን አቋም አስረድተዋል።

ሰኞ ዕለት ትግራይ ውስጥ በተፈጸመ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ቢያንስ 17 ሰዎች መገደላቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን የእርዳታ ሠራተኞች የተናገሩ ሲሆን፤ በጥቃቱ ከተጎዱት መካከል አብዛኞቹ ሴቶች መሆናቸውም ተገልጿል።

በተጨማሪም በደደቢት ከተማ ተፈናቃዮች በተጠለሉበት ካምፕ ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት 56 ሰዎች ባለፈው ሳምንት መገደላቸውም ተዘግቧል።

ከሰሞኑ ተፈጽመው በርካታ ሰዎችን ለሞት የደረጉትን የአየር ጥቃቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት አስካሁን ያለው ነገር የለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአየር ጥቃቱን በተመለከተ ምን አይነት ቃል ገብተዋል ለሚለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትን ለማንበብ ለኢትዮጵያውያን ትቼዋለሁ ብለዋል።

እንዲሁም ዋይት ሐውስም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትክክል ስለተናገሩት ጉዳይን ዝርዝር አስመልክቶ ለራሳቸው የመተው አቋም እንደሚኖረው እገምታለሁ በማለት አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር ያደረጉትን ንግግር አስመልክቶ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ወቅታዊ ጉዳዮች፣ በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ግልጽ ውይይት አድርገዋል።

ጨምረውም ሁለቱ መሪዎች ኢትዮጵያና አሜሪካ በጋራ መከባበር ላይ መሰረት በማደረግ ገንቢ ግንኙነት በማድረግ ትብብራቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን አመልክተዋል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

አስራ አራት ወራት ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ እና ሌሎች አጋሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።