የካናዳዋ ግዛት ባልተከተቡት ላይ የጤና ግብር ልትጥል ነው

የካናዳዋ ኪዩቤክ ግዛት የኮቪድ-19 ክትባት ባልወሰዱ ነዋሪዎቿን የጤና ግብር ልታስከፍል ነው።

ከዚህ ቀደም በካናዳ ካሉ ግዛቶች በወረርሽኙ መስፋፋት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ኩዩቤክ በአሁኑ ወቅትም የቫይረሱ ስርጭት አይሎባታል።

ትናንት የክልሉ ገዢ ኪዩቤክ በካናዳ ክትባት ያልወሰዱትን በገንዘብ ስትቀጣ የመጀመሪያዋ ትሆናለች ብለዋል።

እስካሁን ከግዛቷ ነዋሪዎች 12.8 በመቶ ብቻ የሚሆኑት ነዋሪዎች ናቸው ክትባቱን ያልወሰዱት። ይሁን እንጂ በኮቪድ ተይዘው ሆስፒታል ከሚገቡት ወደ ግማሽ የሚጠጉት ያልተከተቡ ሰዎች ናቸው።

የግዛቷ አስተዳዳሪ ፍራንኮኢስ ሌጋኡለተ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የመጀመሪያ ዙር ክትባት ያልወሰዱ ሰዎች "መዋጮ" መክፈል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የክፍያ መጠኑ ባይገለጽም፤ ክፍያው "ቀላል" እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ግዛቷ የኮቪድ ስርጭቱን ለመግታት የሰዓት እላፊ ገደብ አስተዋውቃለች እንዲሁም ሰዎች አገልግሎት ፍለጋ ተቋማትን ከመጎብኘታቸው በፊት የክትባት ማስረጃ እንዲያሳዩ ትጠይቃለች።

ይህ የግዛቱ አስተዳዳሪዎች ውሳኔ የተሰማው ባለፉት 24 ሰዓታት በኪዩቤክ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የ62 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ከተገለጸ በኋላ ነው።

8ሺህ 710 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። በአሁኑ ወቅት ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ 2ሺህ 742 ሰዎች ሆስፒታል የገቡ ሲሆን 244 የሚሆኑት በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ።

ኪዩቤክ ክትባት ባልወሰዱት ላይ የገንዘብ መቀጮ ያስተዋወቀች ብቸኛዋ አይደለችም።

አውሮፓዊቷ ግሪክ ከሳምንታት በኋላ ክትባት ያልወሰዱ እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆነቸው ሰዎችን በየወሩ 100 ዩሮ ክትባት እስኪወስዱ ድረስ እንዲከፍሉ ውሳኔ አስተላልፋለች።

ሲንጋፖር ደግሞ የኮቪድ ክትባት ያልወሰዱ ሰዎች የጤና ክፍያዎችን ከኪሳቸው እንዲሸፍኑ አዛለች።