ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከኮቪድ ምርመራ ውጤት ውዝግብ ጋር በተያያዘ ኬንያ ከአረብ ኤምሬትስ የሚደረጉ በረራዎችን አገደች
ኬንያ ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ በቀጥታም ሆነ በትራንዚት የሚደረጉ የመንገደኞች አውሮፕላን በረራዎችን ለሰባት ቀናት ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ ማገዷ ተነገረ።
እገዳው ከትናንት ሰኞ ጀምሮ በዚህ ሳምንት ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆንም ተገልጿል።
የኬንያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ይህን እገዳ ተግባራዊ የሚያደርገው ዩናይትድ አረብ አምሬትስ ከኬንያ በሚነሱ በረራዎች ላይ ለጣለችው እገዳ ምለሽ ለመስጠት ነው ብሏል።
ነገር ግን የተጣለው እገዳ በመንገደኛ አውሮፕላኖች ላይ ሲሆን የጭነት በረራዎችን የሚመለከት ባለመሆኑ ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የሚነሱ የጭነት አውሮፕላኖች ሥራቸውን ይቀጥላሉ።
ባለፈው ታኅሣሥ ወር የዱባይ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከኬንያ የሚነሱ እና ትራንዚት የሚያደርጉ አውሮፕላኖች ላይ ክልከላ መጣሉ ይታወሳል።
የዱባይ የአየር ትራንስፖርት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ለዚህ እርምጃቸው እንደ ምክንያት ያቀረቡት ከኬንያ የሚነሱ መንገደኞች ምንም እንኳን ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆናቸውን የሚያመለክት ሰርተፊኬት ቢይዙም፤ በመዳረሻቸው በተደረገላቸው ምርመራ ቫይረሱ ስለተገኘባቸው ነው።
የኬንያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዳይሬክተር ጀነራል ጊልበርት ኪቤ ከኬንያ ወደ ዱባይ የሚጓዙ መንገደኞች መንግሥታዊ ካልሆኑ የኮቪድ መርመራ ማዕከላት ጋር በመመሳጠር ሐሰተኛ የኮቪድ-19 ፒሲአር ሰርተፊኬት እየተቀበሉ ስለመሆኑ መረጃው አለ ሲሉ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
የኬንያ ጤና ሚንስቴር ጉዳዩን እየመረመርኩ ነው ብሏል።
አዲሱ የኮቪድ ዝርያ ኦሚክሮን መስፋፋትን ተከትሎ ባለፉት 14 ቀናት ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ከበርካታ የደቡብ አፍሪካ አገራትን የሚደረጉ የመንገደኞች በረራዎች ላይ እገዳ ጥላለች።