ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካዊው በንቅለ ተከላ በዘረ መል ምህንድስና የተሻሻለ የአሳማ ልብ በማግኘት በዓለም የመጀመሪያው ሆነ
አሜሪካዊው ግለሰብ በንቅለ ተከላ በዘረ መል ምህንድስና (ጄኔቲክ ኢንጂኔሪንግ) የተሻሻለ የአሳማ ልብ በማግኘት ከዓለም የመጀመሪያው ሆነ።
የ57 ዓመቱ ዴቪድ ቤኔት በባልቲሞር ሰባት ሰዓት የፈጀ ቀዶ ሕክምና ከተደረገለት ከሦስት ቀናት በኋላ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ሐኪሞቹ ተናግረዋል።
ምንም እንኳን የቤኔት የረዥም ጊዜ የጤና ሁኔታው ምን እንደሚሆን ግልጽ ባይሆንም ንቅለ ተከላው ሕይወቱን የማዳን የመጨረሻ ተስፋ ተደርጎ ነበር የተወሰደው።
"ንቅለ ተከላውን ማድረግ አሊያም መሞት ነበረብኝ" ሲል ቤኔት ከቀዶ ሕክምናው አንድ ቀን በፊት ስለነበረበት ሁኔታ ተናግሮ ነበር።
"በጨለማ ውስጥ ጥይት የመተኮስ ያህል እንደሆነ አውቃለሁ፤ ግን ይህ የመጨረሻ ምርጫዬ ነው" ብሏል ቤኔት።
በሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ማዕከል ሐኪሞች ቤኔት ሊሞት ይችላል በሚል ሕክምናውን እንዲያደርጉ ከአሜሪካ የሕክምና ተቆጣጣሪ ልዩ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል። ይህ ውሳኔ በሐኪሞች የሚወሰነው ህመምተኛው የከፋ ጤንነት ላይ በሚሆንበት ጊዜ ነው።
ይህም ንቅለ ተከላውን ላደረጉት የሐኪሞች ቡድን ለዓመታት ሲካሄድ የነበረው ምርምር መጨረሻን ያመላከተ ሲሆን በዓለም ዙሪያ የሰው ልጅ ሕይወትን ሊለውጥ ይችላል ተብሏል።
የሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ክፍል ባወጣው መግለጫ ፤የቀዶ ሕክምና ሐኪሙ ባርትሌይ ግሪፍዝ "ቀዶ ሕክምናው በዓለማችን የሚያጋጥመውን የአካል ክፍሎችን እጥረት ለመፍታት አንድ እርምጃ ወደፊት ያስጠጋ ነው" ብለዋል።
በአሜሪካ በአንድ ቀን 17 ሰዎች ንቅለ ተከላ ለማድረግ እየተጠባበቁ ሕይወታቻው ያልፋል። ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎችም ተመዝግበው ተራቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
ይህንን ፍላጎት ለማሟላትም 'ዜኖትራንስፕላንቴሽን' በሚባለው የእንስሳትን የአካል ክፍል ወደ ሰው በንቅለ ተከላ በመተካት ለመጠቀም ለረዥም ጊዜ ሲታሰብበት ቆይቷል። በመሆኑም የአሳማ ልብ የደም ቧንቧዎችን መጠቀም ቀድሞውኑም የተለመደ ነው።
ጥቅምት ወር ላይ በኒውዮርክ የሚገኙ የቀዶ ሕክምና ሐኪሞች በንቅለ ተከላ የአሳማ ኩላሊት በተሳካ ሁኔታ ለሰው መትከላቸውን አስታውቀዋል። በወቅቱ ቀዶ ሕክምና በዘርፉ የተደረገ የላቀ ሙከራ ነበር።
ይሁን እንጂ ህመምተኛው የመዳን ተስፋ ሳይኖረው አእምሮው ሥራውን አቁሞ በሰው ሰራሽ ድጋፍ ይገኛል።
ቤኔት ግን ንቅለ ተካላው ሕይወቱን እንዲቀጥል እንደሚያስችለው ተስፋ ሰንቋል። ከቀዶ ሕክምናው በፊት ለስድስት ሳምንታት የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ነበር። የልብ ህመም እንዳለበት ከታወቀም በኋላ በሕይወት እንዲቆይ የሚያስችለውን ማሽን መጠቀም ጀምሯል።
"ካገገምኩ በኋላ ከአልጋየ ለመነሳት በጉጉት እጠብቃለሁ" ሲልም ቤኔት ባለፈው ሳምንት ተናግሯል።
ሰኞ ዕለት ቤኔት በከፍተኛ ክትትል ውስጥ ሆኖ በራሱ መተንፈስ መቻሉ ተነግሯል።
ይሁን እንጂ በቀጣይ ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽ አይደለም።
የቀዶ ሕክምና ሐኪሙ ግሪፍዝ፣ ቤኔትን በጥንቃቄ እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሆኖም ልጁ ዴቪድ ቤኔት "አሁን ቤተሰቡ ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ" ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግሯል።
ዴቪድ አክሎም የተሰራውን ንቅለ ተከላ ክብደት እንዲሁም አስፈላጊነት እንደሚገነዘብ ገልጿል።
ግሪፊዝ " ይህንን በሰው ላይ አድርገን አናውቅም፤ ይህንን በማድረጋችን ደስ ብሎኛል። የተሻለ አማራጭ ሰጥተነዋል" ብለዋል። "ግን ለአንድ ቀን ፣ ለሳምንት፣ ለወር አሊያም ለዓመት ይኑር አይኑር አላውቅም" ብለዋል ግሪፊዝ።