አቶ ስብሐት ነጋና ሌሎች ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች በምህረት እንዲፈቱ ተወሰነ

አቶ ስብሐት ነጋን ጨምሮ ከፍተኛ የቀድሞ የህወሓት አመራሮች በምህረት ከእስር እንዲፈቱ መወሰኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አግልሎት አስታወቀ።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በፌደራል መንግሥቱ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ ከነበሩት የህወሓት አመራሮች መካከል የድርጅቱ መስራች የነበሩት አቶ ስብሐት ነጋና ሌሎች አምስት የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ናቸው በምህረት የሚፈቱት።

በዚህም መሠረት አቶ ስብሐት ነጋ፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ፣ አቶ ዓባይ ወልዱ፣ አቶ አባዲ ዘሙ፣ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር፣ አቶ ኪሮስ ሐጎስ በምህረት እንዲፈቱ መወሰኑን መንግሥት አስታውቋል።

በተጨማሪም የተቃዋሚ ፖለቲከኞቹን አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በእሱ መዝገብ ስር የተከሰሱ ግለሰቦች በምህርት እንዲለቀቁ መወሰኑ ተገልጿል።

ቢቢሲ ቀደም ብሎ እንደዘገበው አቶ ጃዋርና ሌሎችም ታሳሪዎች ከአስር ቤት እንዲወጡ የተነገራቸው ሲሆን ጊዜው በመምሸቱ አለመውጣታቸውን ጠበቃቸው ገልጸው ነበር።

አቶ አስክንድር ነጋ እና በእሳቸው መዝገብ ከተከሰሱት መካከል አቶ አስክንድርና አቶ ስንታየሁ ቸኮል ከአስር ቤት መውጣታቸውን አቶ ስንታየሁ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የምህረት ውሳኔውን በተመለከተ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት "ኢትዮጵያ ለዘላቂ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የትኛውንም መሥዋዕትነት ትከፍላለች" በሚል ባወጣው መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ችግሮችን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ መፍታት እንደሚገባ መንግሥት በጽኑ እንደሚያምን አመልክቷል።

ለዚህም መንግሥት አካታች አገራዊ ምክክር እንዲሳካ ከሚጠበቅበት ሞራላዊ ግዴታዎች አንዱ ምህረት መሆኑን በመጥቀስ "ለተሻለ ፖለቲካዊ ምኅዳር ሲባል የተወሰኑ እሥረኞችን መንግሥት በምህረት ከእሥር ፈትቷል" ብሏል።

ይህ ምህረት ከዚህ በፊት በተፈጸመ ጥፋት የታሠሩትንም ሆነ በቅርቡ ከተፈጠረው ጦርነት ጋር በተያያዘ የታሠሩትን እንደሚጨምርም ጠቅሷል።

ጨምሮም የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋትና ለአካታች አገራዊ ምክክር ሲባል በምህረት የተፈቱት ግለሰቦች "ካለፈው የጥፋት መንገድ ተምረው፣ የተሻለ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አስተዋጽዖ በማድረግ፣ አገራቸውንና ሕዝባቸውን ይክሳሉ" ብሎ መንግሥት እንደሚያምን ተገልጿል።

መንግሥት ይህንን ውሳኔ የወሰነው "የኢትዮጵያን ችግሮች ሰላማዊ በሆነ፣ ከእልክና ከመጠፋፋት በራቀ ሁኔታ፣ በአገራዊ ምክክር በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል መንገድ ለመክፈት" መሆኑን ጠቅሶ፤ ለዘመናት የቆዩ ፖለቲካዊ ችግሮችን በአካታች ምክክር ለመፍታት እንዲቻል መንግሥት ገለልተኛ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም እየሰራ እንደሚገኝም አስታውሷል።

መግለጫው አክሎም ፍትሕና ምህረት ሚዛናቸው እንዲጠበቅ መንግሥት እንደሚፈልግና በሂደቱ የተጎዱ ዜጎች "ቁስል በሽግግር ፍትሕ የሚካስ ይሆናል" ብሏል።

የፍትህ ሚኒስቴር ከአመሻሹ ባወጣው መግለጫ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሕገ-መንግስት እና የሽብር ችሎት እየታየ ከነበሩት ተከሳሾች መካከል በነጃዋር ሲራጅ መሃመድ እና በእነ እስክንድር ነጋ ፈንታ መዝገብ ያሉ ተከሳሾች ክሳቸው በአዋጅ ቁጥር 943/2008 መሰረት እንዲነሳ ተደርጓል ብሏል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ባሰፈረው መሰረት ክሱ እንዲነሳ የተደረገው" በቀጣይ የሚደረገውን ሃገራዊ የምክክር መድረክ ሂደት ውጤታማነት እና አካታችነት ከፍ ለማድረግ በማሰብ ነው።" ብሏል።

በተጨማሪም በእነ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መዝገብ ክስ ከቀረበባቸው ውስጥ የጤና እና የዕድሜ ሁኔታን ከግምት በማስገባት የስድስት ግለሰቦች ክስ እንዲነሳ ተደርጓል ብሏል።