ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮቪድ-19 ፡ የኮሮና ለክትባት አንወስድም ያሉ ከ100 በላይ የአሜሪካ ወታደሮች ከሠራዊቱ ተገለሉ
የኮሮናቫይረስ ክትባት አንወስድም ያሉ ከአንድ መቶ በላይ የአሜሪካ ወታደሮች ከሠራዊቱ መገለላቸው ተነገረ።
የአሜሪካ ወታደሮችና ሌሎች የሠራዊቱ አባላት ክትባት ለመውሰድ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ከቀሩ ከጦር ኃይሉ በክብር ወይም ሙሉ ለሙሉ ይሰናበታሉ።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አብዛኞቹ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት አባላት የኮቪድ ክትባትን የወሰዱ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ግን ክትባቱን ላለመውሰድ ተቃውመዋል።
እስካሁን እስከ 20,000 የሚደርሱ ወታደሮች ክትባቱ እንዲቀርላቸው ጠይቀዋል ወይም መከተብን ተቃውመዋል።
የጦር ሠራዊቱ ከፍተኛ አካል እስከዚህ ወር መጨረሻ ድረስ በሥራ ላይ ያሉ ሁሉም ወታደሮች ክትባቱን እንዲወስዱ ቀነ ገደብ ያስቀመጠ ሲሆን እስካሁን 103 ሰዎች ከሥራ መገለላቸው ታውቋል።
እንደ ማሪን ኮርፕ ታይምስ ጋዜጣ ዘገባ 95 በመቶ የሚሆነው የአገልግሎቱ አባላት ሙሉ በሙሉ የተከተቡ ሲሆን እስካሁን 1ሺ 7 ሰዎች ደግሞ ላለመከተብ ያቀረቧቸው ምክንያቶች ተቀባይነት አግኝተዋል።
በተጨማሪም ከ 3,000 በላይ የባህር ኃይል ወታደሮች ሃይማኖታዊ ምክንያት በማቅረብ ላለመከተብ አመልክተዋል። እስካሁን ከ2 ሺህ 800 በላይ የሚሆኑት ጉዳያቸው የታየላቸው ሲሆን አንዳቸውም ምክንያታቸው ተቀባይነት አላገኘም፡
የአሜሪካ ትልቁ ወታደራዊ ቅርንጫፍ እስካሁን 98 በመቶ የሚሆኑ በሥራ ላይ ያሉ ወታደሮቹ ቢያንስ የመጀመሪያውን ዙር ክትባት ወስደዋል። 96 በመቶ የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ የተከተቡ ናቸው።
ጦሩ ክትባቱን አንወስድም ያሉ ሁለት የሻለቃ አዛዦችን ጨምሮ ስድስት ከፍተኛ መኮንኖችንም ከሥራ አግልሏል። ከ2,700 በላይ የሠራዊቱ አባላት የጽሁፍ ማጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። በእንቢተኝነታቸው የሚጸኑትን በቀጣዩ ወር ጀምሮ ከሥራቸው እንዲገለሉ ያደርጋል።
በጦር ውስጥ በግዳጅ ላይ ካሉ ከጠቅላላው አባላት ከአንድ በመቶ በታች የሚሆኑት ውይም 3 ሺህ 864 ወታደሮች ለሌላ ጊዜ እንዲዘዋወርላቸው ሳይጠይቁ ወይም ምክንያት ሳያቀርቡ ለመከተብ አሻፈረኝ ብለዋል።
ለክትባት በተቀመጠው ቀነ ገደብ ውስጥ 1.7 በመቶ የሚገመተው የባህር ኃይል አባላት ብቻ ክትባት አልወሰዱም።
አየር ኃይሉ በዚህ ሳምንት 27 የአየር ኃይል አባላት ክትባት አንወስድም በማለታቸው ከአገልግሎት መገለላቸውን አስታውቋል። ይህ ጦር በዚህ ወር መግቢያ ላይ ከ97 በመቶ በላይ አባላቱ ክትባት ወስደዋል።
የፔንታጎን የፕሬስ ሴክሬታሪ ጆን ኪርቢ ሐሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ "እስካሁን ያልተከተቡ በሺዎች የሚቆጠሩ የሠራዊቱ አባላት አሁንም ለራሳቸው እና ለዩኒታቸው ትክክለኛውን ተግባር ለመከወን እድሉ አላቸው" ብለዋል ።
ረቡዕ በኮንግረስ የፀደቀው የብሔራዊ መከላከያ ፍቃድ ድንጋጌ ክትባቱን የማይወስዱ ወታደሮች በክብር እንዳይሸኙ የሚከለክል አገላለጽ ጨምሮበታል።