በአላማጣ በርካታ ሰዎች በአየር ጥቃት ተገደሉ ሲሉ የትግራይ አማጺያን ከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Tigtv
በአላማጣ ከተማ በተፈጸመ የአየር ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውን የትግራይ አማጺያን ገለጹ።
በአማጺያኑ ስር ያለው የትግራይ ቴሌቪዥን ሐሙስ ዕለት በአላማጣ ከተፈጸመ ስድስት ዙር የአየር ጥቃቱ በኋላ የነበረ ነው ያለውን ሁኔታ የሚያሳይ ምስል አቅርቧል።
ዘገባው በአየር ጥቃቱ ህጻናትን ጨምሮ 28 ሰዎች መሞታቸውንና 78 የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል ብሏል።
በቴሌቪዥኑ ላይ የቀረበው ቪዲዮ በርካታ ሰዎች መሬት ላይ ወድቀው ያሳየ ሲሆን፣ በርካታ ሰዎች ቆስለው በአላማጣ ሆስፒታል ህክምና ሲደረግላቸው አሳይቷል።
የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው ላይ በርካታ ሰዎችን የገደለ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት በአላማጣ ላይ መፈጸሙን አስፍረዋል።
በአካባቢው የስልክ ግንኙነት በመቋረጡ ጥቃቱን በተመለከተ ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም። የኢንተርኔትና ስልክ አገልግሎት ባለመኖሩ ጋዜጠኞች ወደ አካባቢው መድረስ ስለማይችሉ የቀረበውን ክስ በገለልተኛ ወገን ለማጣራት አዳጋች ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ መከላከያ ሠራዊት ስለተባለው የአየር ጥቃት እስካሁን ያሉት ነገር የለም።
ነገር ግን ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊቱ የሚፈጽመው የአየር ጥቃት ኢላማ የሚያደርገው የአማጺያኑ የማሰልጠኛ ቦታ ወይም የጦር መሳሪያ መከማቻ መሆኑን ገልጿል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የህወሓት ኃይሎች በአገሪቱ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አጎራባቾቹ አፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ ቆይቷል።
በዚህም ሳቢያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው ለመፈናቀል ተገደዋል። የሰብአዊ መብት ቡድኖች በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን ሪፖርት አውጥተዋል።
ሐሙስ ዕለት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይተስ ዋች በጋራ ባወጡት መግለጫ የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች በምዕራብ ትግራይ ውስጥ በሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ የጅምላ እስር፣ የግዳጅ ማፈናቀል እና ግድያን ጨምሮ "አዲስ ተከታታይ ጥቃት" እየፈጸሙ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በሰብአዊ መብት ድርጅቶቹ የቀረበውን ክስ በተመለከተ ለሮይተርስ በሰጡት ምላሽ "መሰረተ ቢስና በማስረጃ ያልተደገፈ" ሲሉ ያጣጣሉት ሲሆን፣ የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ደግሞ ለተፈጸሙ የትኛውም አይነት ጥቃቶች የትግራይ ኃይሎች ተጠያቂ ናቸው ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙት ቆቦ እና ጭና በተባሉ ስፍራዎች በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን በጅምላ መግደላቸውን አመልክቷል።
ዛሬ በአውሮፓ ሕብረት ጠያቂነት ይካሄዳል የተባለው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ፣ በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ በሁሉም ወገኖች የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን የሚያወግዝ የውሳኔ ሐሳብ ያቀርባል ተብሏል።
ይህ የውሳኔ ሐሳብ በምክር ቤቱ ተቀባይነትን ካገኘ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጨማሪ ምርመራ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ኮሚሽን እንዲቋቋም ይጠየቃል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ስብሰባውንና የቀረበውን ሃሳብ የተቃወመው ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አማካይነት የተካሄደውን ምርመራ መሠረት በማድረግ መንግሥት እርምጃ እየወሰደ ባለበት ጊዜ ልዩ ስብሰባ መጥራቱ "ፖለቲካዊ ፍላጎት" አለው ሲል ተቃውሟል።












