ኢትዮጵያ አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሽንድዬን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ያቀረበችውን ጥያቄ ለጊዜው አነሳች

ኢትዮጵያ የአሸንዳ/ ሻደይ/ አሸንድዬ/ አይኒዋሪ/ ማርያ/ ሶለል ባሕላዊ ቅርስን በዩኔስኮ በሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ አቅርባው የነበረውን ጥያቄ ለጊዜው ማንሳቷ ተገለጸ።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ይህችን በትግራይና በአማራ ክልሎች ውስጥ ታዋቂ የሆነችውን ባህላዊ ክንውን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም፣ ዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚያስፈልጉ ሰነዶችን በማቅረብ ነበር ምዝገባ ጥያቄ ያቀረበችው።

ነገር ግን ለምዝገባው የሚያስፈልገውን መስፈርት ለማሟላት በገምጋሚ አካላት ለተነሱ በርካታ ጥያቄዎች ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ምላሽና ማብራሪያ ቢቀርብም በዚህ ዓመት ለሚሰጠው ውሳኔ ሳይደርስ መቅረቱን በቱሪዝም ሚኒስቴር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባለሙያ የሆኑት አቶ ገዛኸኝ ግርማ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ በሰሜን ኢትዮጵያ በሴቶች የምትካሄድ ባህላዊ ክንውን በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ ጥያቄ የቀረበው ከሦስት ዓመት በፊት መሆኑን የገለጹት አቶ ገዛኽኝ፣ በተለያዩ ጊዜያት በቀረቡ ሰነዶች ላይ ከገምጋሚ ባለሙያዎች ጥያቄ ቀርቦ ማብራሪያ መሰጠቱን ተናግረዋል።

ገምጋሚ ባለሙያዎቹ ይህንን ባህላዊ ቅርስ ለመመዝገብ በቀረበው ሰንድ ላይ መሟላት ካለባቸው አምስት መስፈርቶች አራቱ አለመሟላታቸውን ቢገልጹም በኢትዮጵያ በኩል ግን አስፈላጊውን መረጃ አሟልታ ማቅረቧ ተገልጾ ነበር።

ቀደም ሲል አገሪቱ ላስመዘገበቻቸው ባሕላዊና ታሪካዊ ቅርሶች እንደተደረገው ሁሉ ለአሸንድዬ አስፈላጊውን ምላሽ የሚሰጡ ሰነዶች ተዘጋጅተው የቀረቡ ቢሆንም መስፈርቶችና የተካሄደው ግምገማ ለየት ያለ ነበር ብለዋል ባለሙያው።

በዚህም ከአሸንድዬ ጋር በተያያዘ በቀረበው የቅርሱ የማስመረጫ ሰነድ ላይ ምላሽ አልተሰጠባቸውም የተባሉት ጉዳዮች የሰብአዊ መብቶችንና የጾታ እኩልነትን እንደሚያስከብበር አያሳይም እንዲሁም ቅርሱ ተመዝግቦ የቱሪስት ቁጥር ሲጨምር ባህላዊና ማኅበራዊ እሴትን በሚያስጠብቅ መንገድ እንደሚቆይ አለማመልከቱና ቅርሱ እንዲመዘገብ የማኅበረሰቦች ይሁንታ መገኘት የሚሉት ይገኙበታል።

የቅርስ ጥበቃና ጥናት በበኩሉ ይህች በዓል በዋነኝነት ሴቶች ጎልተው የሚታዩበት በዓል መሆኑ፣ ይህም ባህላዊና ማኅበራዊ እሴት ተጠብቆ እንዲቆይ አስፈላጊው ነገር እንደሚደረግና በዓለም ደረጃ እንዲመዘገብ የማኅበረሰቦቹ ፍላጎት መሆኑን የሚያመለክት ፊርማ ጭምር መቅረቡን ገልጿል።

ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ባስመዘገበቻቸው የማይዳሰሱ ቅርሶች ሂደት ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው አቶ ገዛኸኝ ግን ተቋማቸው ካለው ልምድ በመነሳት አስፈላጊውን መረጃና ማብራሪያ መቅረቡንም አመልክተዋል።

ነገር ግን ኢትዮጵያ የአሸንዳ/ ሻደይ/ አሸንድዬ/ አይኒዋሪ/ ማርያ/ ሶለል ባህላዊ ቅርስ ምዝገባ ያቀረበችውን ጥያቄ ለጊዜው በማንሳት ለግምገማው የሚያስፈልጉ ሰነዶችን መልሳ በማደረጃት ጥያቄውን በድጋሚ እንደምታቀርብ አቶ ገዛኸኝ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ይህችን ታሪካዊ ትውፊት በቅርስነት ይመዝገብልኝ በማለት ለተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት፣ ዩኔስኮ ከዓመታት በፊት ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን ታኅሣሥ 06/2014 ዓ.ም በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ በሚደረገው ዝግጅት መልስ ይሰጠዋል ተብሎ ነበር።

ኢትዮጵያ ለዩኔስኮ ባስገባችው ሰነድ መሰረት የክብረ በዓሏን ዳራ፣ ማኅበራዊ ክንውኖች፣ የቅርሷ ባለቤቶች፣ አፋዊ ትውፊቶችና መገለጫዎችን በተመለከተ በዝርዝር መረጃ አያይዛለች።

ከዚህም በተጨማሪ የቅርሱ ዋነኛ ባለቤት ማኅበረሰቦችን ማንነት፣ የቅርሱ አስፈላጊነትና ጠቀሜታንም የመሳሰሉ መረጃዎችን አጠናቅራለች።

ኢትዮጵያ በብሔራዊ ደረጃ አሸንዳ/ ሻደይ/ አሸንድዬ/ አይኒዋሪ/ ማርያ/ ሶለልን በቅርስና ጥናትና ጥበቃ አማካኝነት በቅርስነት የመዘገበችው ነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም ነው።

በወቅቱም ከሁለቱ ክልሎች በርካታ ጥናትና መረጃዎችን እንደተጠናቀሩና በዩኔስኮም ለማስመዝገብ ይቻል ዘንድ እኚሁ መረጃዎች ማቅረባቸው ተገልጾ ነበር።

በተለያዩ ስፍራዎች ዘንድ የተለያየ መጠሪያ ያላት ይህች ክብረ በዓል በትግራይና በአማራ ክልል የሚገኙ ሴቶች በመንገዶችና አደባባዮች ላይ በመውጣት ነፃነታቸውን የሚያውጁባት እንደሆነች ይነገራል።

ለሴቶችና በሴቶች የምትዘጋጅ ክብረ በዓል እንደሆነች ኢትዮጵያ ለዩኔስኮ ባስገባችው ሰነድ የገለጸች ሲሆን ሴቶች በቡድን ሆነው ወገባቸው ላይ የአሸንዳ/ ሻደይ፣ አሸንድዬ ተክል አስረው የሚጫወቱባት እንደ ባህላዊ የሴቶች ነፃነት ቀን የምትከበር የአደባባይ ክብረ በዓል ናት።

የበዓሉ ዝግጅት ከስፍራ ስፍራ ቢለያይም በዋናነት ከነሐሴ 16 ጀምሮ ለሶስት ቀናት በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ዝግጅቱ ከሁለት ሳምንት እስከ አንድ ወር ቀደም ብሎ ይጀመራል።

በአማራ ክልል ዋግ ኸምራ አካባቢ ሻደይ፣ በላስታ ላሊባላና ጎንደር አካባቢዎች አሸንድዬ እንዲሁም በራያ ቆቦ ሶለል በመባል የምትጠራ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል እንደርታ እና ተንቤን አካባቢዎች አሸንዳ፣ በአክሱም አይኒዋሪ እና በአዲግራት ማርያ ትባላለች።

የበዓሉ ስያሜ በትግራይና በአማራ ክልሎች ሴቶች ወገባቸው ላይ ከሚያስሩት ተክል መጠሪያ በመነሳት አሸንዳ፣ አሸንድዬና ሻደይ በሚል በትግርኛ፣ በአማርኛና በኽምጠኛ ቋንቋዎች መጠሪያዋን አግኝታለች።

በምስራቅ ራያ ቆቦ አካባቢ ከግዕዝ ቋንቋ በመውሰድ ሶለል፣ በማዕከላዊ ትግራይ አክሱም ዋሪ ከምትባል ወፍ መጠሪያዋን አግኝታ አይኒ ዋሪ እንዲሁም በምስራቅ አዲግራት አካባቢ ደግሞ ማርያ ትባላለች።

አሸንዳ፣ ሻደይ አሸንድዬ የሁለት ነገሮች ስያሜ ስትሆን የመጀመሪያው በበዓሉ ወቅት ሴቶች ተልትለው በገመድ ወገባቸው ላይ የሚያስሩት ስሩ ነጭ ሆኖ ሌላው ክፍል አረንጓዴ የሆነ የኮባ ቅጠል የመሰለ ተክል ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሴቶች በቡድን በቡድን እየሆኑ የሚጫወቷት ባህላዊ ጨዋታ ስያሜ ናት።

የበዓ መሰረት

በዓሉ በትግራይና በአማራ አካበቢዎች በድምቀት የምትከበር ቢሆንም የበዓሉ አመጣጥ ላይ የተለያዩ ታሪካዊ፣ ባህላዊና እምነታዊ ጉዳዮች አሉ።

ከቅድመ ልደተ ከርስቶስ ጀምሮ የክረምቱን መውጣትና የበጋውን መምጣት በደስታና በሀሴት መቀበላቸውን ለማስታወስ የሚያከብሯት በዓል መረጃዎች ቢኖሩም ሌሎች ደግሞ ከክርስትና ሃይማኖት ጋር የተያያዘች እንደሆነችና በዓሉ በሚከወንባቸው አካባቢዎች የክርስትና እምነት ከተስፋፋ በኋላ መከበር እንደተጀመረች የታሪክ ድርሳናትን በማጣቀስ ያስረዳሉ።

የበዓሏን አመጣጥ ከክርስትና እምነት ጋር የሚያይዙት መሰረቱ ማርያም ያረገችበት/ የፈለስችበት ዕለትና የፍልሰታ ፆም ማብቂያ ነሐሴ 16 ዕለትን ሲሆን በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በዓለ ዕርገት በመባል ይታወቃል። በዚህም መሰረት አሸንዳ/ ሻደይ/ አሸንድዬ/አይኒዋሪ/ ማሪያ/ ሶለል መሰረቱ የማርያም በዓል ነው ይላኡ።

የበዓሏ መነሻ ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው የሚሉ ደግሞ በኖህ ዘመን የጥፋት ውሃ መጉደሉን ለማብሰር እርግቧ ይዛ የመጣችውን ለምለም የወይራ ቅጠል መሰረት በማድረግ የመፅሀፍ ቅዱስን ታሪክ ያጣቅሳሉ።

ሌሎች ደግሞ እንዲሁ መፅሀፍ ቅዱስን መነሻ በማድረግ የዮፍታሔ ልጅ አባቷ ሊሰዋት እንደሆነ ሲነግራት ከጓደኞቿ ጋር በመሆን ቅጠሉን ታጥቀው የስንብትና የሙሾን ዝማሬ ያቀረቡበትን በመዘከር ነው ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ ኢትዮጵያውያን አዲስ አመት ከሚያከብሩት ከቀናት በፊት መከበሯን በማያያዝ መነሻው ይኸው ነው ይላሉ። በዓሏ የአዲስ ዘመን መምጣትን ማብሰሪያ ክረምቱና የክረምቱ ችግሮች እያለቁ መሆኑን እና አዲስ ዘመን መምጣቱን ሴቶች በየቤቱ እየዞሩ የሚያበስሩበት ባህላዊ ጨዋታ ነውም ይባላል።

ምንም እንኳን አመጣጡ ከክርስትና እምነት ጋር ቢያያዝም ባህላዊ ትውፊቱን በማስታወስ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች በጋራ የሚያከብሩት በዓል ነው።

ክብረ በዓሏን አስመልክቶ በሃገር ደረጃ በቅርስነት ለመመዝገብ የተሰራ ኢንቨንቴሪ ላይ እንደሚያትተው የትግራይ እና የአማራ ህዝቦችን የሚያስተሳስር የጋራ ባህላዊ እሴት ናት ይላል።

ከዚህም በተጨማሪ የቅርሷ አስፈላጊነትና ጠቃሚነት ላይም ማህበራዊ ፋይዳ በሚልም"የእድሜ እኩያዎች እርስ በርስ እንዲገናኙ ፣ ፍቅር እንዲኖር፣ መነፋፈቅ እንዲጎለብት፣ ማህበራዊ ግንኙነት እንዲጠነክር በአጠቃላይ በዓሏን የጋራ አድርጎ በአንድ መንፈስ ከመንቀሳቀስና ባህላዊ እሴቱን ከማጎልበት አንፃር" ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላት አስፍሯል።

ከዚህም በተጨማሪ ይኸው ሰነድ ፖለቲካዊ ፋይዳ ብሎ ያሰፈረው "በዓሏ ሴቶች የሚዋቡበትና ወደ ውጭ ወጥተው የማያውቁም መጥተው እንዲጫወቱ ፈቃድ የሚያገኙበት በመሆኑ ይህ ወቅት ለሴቶች የነፃነት ቀን ነው። በጨዋታው ሴቶቹ ያለማንም ጣልቃ ገብነት አለቃቸውን በነፃነት ስለሚመርጡ ዲሞክራሲያዊ ምርጫን የሚተገብሩበት ነው" በማለትም አትቷል።

ጥቂት ስለ ዩኔስኮ ስብሰባ

አስራ ስድስተኛው የበይነ መንግሥታዊ የማይዳሰሱ የባህል ቅርሶች ጥበቃ ኮሚቴ በፓሪስ በበይነ መረብ ከታህሳስ 4 ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን ታህሳስ 9 ድረስ ይቀጥላል።

በዚህ ስብሰባ ላይ የመንግሥታት ተወካዮች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የባህል ተቋማትን እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሚሳተፉበት ነው።

የዩኔስኮ ድረ-ገፅ መረጃ እንደሚያትተው ኮሚቴው በሰው ልጅ የማይዳሰሱ የባህል ቅርሶች ወካይ ለመካተት 48 ፋይሎች ቀርበውለታል።

ስድስት ቅርሶች ደግሞ በሰው ልጅ የማይዳሰሱ የባህል ቅርሶች ጥበቃ እንዲደረግላቸው እንዲሁም አምስት የመልካም ጥበቃ ተግባራት ምዝገባ እና ሶስቱ ድግሞ በጅቡቲ፣ ሞንጎሊያ እና ቲሞር-ሌስቴ አገራት የቀረቡ ከ100 ሺህ ዶላር በላይ የአለም አቀፍ እርዳታ ጥያቄዎች ነው።