የዓመቱ የአፍሪካ ምርጥ ስፖርተኛ ዕጩዎች ይፋ ሆኑ

በአፍሪካዊያን እና ዩናይትድ ኪንግደም በሚገኙ ጋዜጠኞች የተመለመሉት ስድስቱ የቢቢሲ የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ስፖርተኞች ዝርዝር ይፋ ሆኗል።

የጋዜጠኞቹ ጉባዔ ስድስት ዕጩዎችን ይፋ ያደረገ ሲሆን ስፖርተኞች በ2021 በዓለም አቀፍ መድረክ አፍሪካን ያስጠሩ ናቸው።

እነሆ የዕጩዎቹ ዝርዝር፡

  • ኢሊዩድ ኪፕቾጌ - አትሌቲክስ
  • ፌይዝ ኪፕዬጎን - አትሌቲክስ
  • ኡንታንዶ ማሽላንጉ በፓራ - አትሌቲክስ
  • ታቲያና ስኩንማርከር - ውሃ ዋና
  • ክሪስቲን ምቦማ - አትሌቲክስ
  • ኤድዋርዶ ሜንዲ - እግር ኳስ

እርስዎም የዘንድሮው ሽልማት ይገባዋል ለሚሉት ዕጬ ድምፅዎን እዚህ መስጠት ይችላሉ።

ድምፅ መስጫው ሰዓት የሚያበቃው ታኅሣሥ 11 ከሌሊቱ 9 ሰዓት ሲሆን የሽልማቱ አሸናፊ ታኅሣሥ 29 በፎከስ ኦን አፍሪካ ቴሌቪዥንና ራድዮ እንዲሁም በቢቢሲ ስፖርት ድረ-ገፅ ላይ ይፋ ይደረጋል።

ዕጩዎቹን በዝርዝር ስንመለከት

ኢሊዩድ ኪፕቾጌ

አገር፡ ኬንያ

ዕድሜ፡ 37

የሩጫ መስክ፡ ማራቶን

ኪፕቾጌ በማራቶን ሩጫ እስከዛሬ ከታዩ አትሌቶች ምርጡ ነው ሲባል ይደመጣል። ኪፕቾጌ በሁለት ተከታታይ ኦሊምፒኮች በማራቶን ውድድር ወርቅ ማምጣት ችሏል።

ኬንያዊው አትሌት በኦሊምፒክ ታሪክ በተከታታይ ማራቶን ያሸነፈ ሦስተኛው ሯጭ ሲሆን በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርጥ ወንድ አትሌት ተብሎም ተመርጧል።

በቶኪዮ ኦሊምፒክ ድል ያስመዘገበው ኪፕቾጌ 15 ጊዜ ማራቶን ሮጦ 13 ጊዜ ድል ማድረግ ችሏል። ከእነዚህ መካከል የርቀቱን ክብረ ወሰን በ2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ39 ሰከንድ የያዘበት የበርሊን ማራቶን ተጠቃሽ ነው።

ፌይዝ ኪፕጎን

አገር፡ ኬንያ

ዕድሜ፡ 27

የሩጫ መስክ፡ መካከለኛ ርቀት

ፌይዝ በቶኪዮ ኦሊምፒክስ በ1500 የውድድሩን ክብረ ወሰን መስበር ችላለች። በዚህ ርቀት በሪዮ የመጀመሪያዋን ወርቅ ማምጣቷም አይዘነጋም።

በወሊድ ምክንያት ከ21 ወራት በኋላ ወደ ሩጫ መድረክ የተመለሰችው ፌይዝ ከወሊድ በኋላ በተመሳሳይ ርቀት ያሸነፈች በታሪክ ሦስተኛዋ አትሌት ሆናለች።

ባለፈው ሐምሌ ሞናኮ በተረገ ውድድር በታሪክ አራተኛውን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገቧ ይታወሳል።

የፌይዝ ቀጣይ ዓላማዋ የርቀቱን የዓለም ክብረ ወሰን መጨበጥ ነው።

ኡንታንዶ ማሽላንጉ

አገር፡ ደቡብ አፍሪካዊ

ዕድሜ፡ 19

የስፖርት መስክ፡ ዝላይና 200 ሜትር ሩጫ

ማሽላንጉ በፓራሊምፒክ ውድድር የመጀመሪያውን ሜዳሊያ ያገኘው የ14 ታዳጊ ሳለ ነበር። በያዝነው ዓመት በ200 ሜትር [ቲ61] እና በዝላይ [ቲ63] ውድድሮች ወርቅ ማምጣት ችሏል።

ደቡብ አፍሪካዊው አትሌት በ7.17 ሜትር ዝላይ የዓለም ክብረ ወሰንን ሰብሯል።

ወደፊት ብዙ ስኬቶች የሚጠብቁት ወጣቱ አትሌት የ10 ዓመት ታዳጊ ሳለ ነበር እግሮቹን ያጣው። ማሽላንጉ ባለፈው ሚያዚያ በ22.94 ሰከንድ የ200 ሜትር የዓለም የወንዶች ክብረ ወሰንን ጨብጧል።

ክሪስቲን ምቦማ

አገር፡ ናሚቢያ

ዕድሜ፡ 18

የስፖርት መስክ፡ አጭር ርቀት

በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ተሳታፊ የነበረችው ክሪስቲን በኦሊምፒክ የአሸናፊዎች መድረክ ላይ በመቆም የመጀመሪያዋ ናሚቢያዊት ሆናለች።

በ25 ዓመታት የናሚቢያ ኦሊምፒክ ታሪክ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ ያስገኘችው ክሪስቲን በ200 ሜትር ርቀት የጃማይካዋ ኦሊምፒክ ቻምፒዮን ኢለይን ቶምፕሰን-ሄራንን ተከትላ በመግባት ብር አግኝታለች።

ክሪስቲን የገባችበት 21.81 ሰከንድ በርቀቱ ከ20 ዓመት በታች ፈጣኑ ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦላታል።

ባለፈው መስከረም ዙሪክ በተካሄደው ዳይመንድ ሊግ በ21.78 ሰከንድ ከማሸነፏም በላይ የአፍሪካ ክብረ ወሰንን ሰብራለች።

የ18 ዓመቷ ታዳጊ በ400 ሜትር በዓለም አትሌቲክስ እንዳትሳተፍ የታገደች በተፈጥሮ ባላት ከፍተኝ ቴስቴስትሮን ምክንያት ነው።

ኤድዋርዶ ሜንዲ

አገር፡ ሴኔጋል

ዕድሜ፡ 29

የስፖርት መስክ፡ እግር ኳስ

ኤድዋርድ ሜንዲ ከፈረንሳዩ ክለብ ሬኔስ ወደ ቼልሲ ከተዛዋረ በኋላ በስታንፈርድ ብሪጅ ብቃቱን ማሳየት ችሏል። ባለፈው ግንቦት ደግሞ የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ በማንሳት ታሪክ ፅፏል።

ወደ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ባደረገው ግስጋሴ ስምንት ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርበት በመጠበቁ ታሪክ ተጋርቷል። ሜንዲ በቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ የተጫወተ የመጀመሪያው ግብ ጠባቂም መሆን ችሏል።

ከዚህ በፊት በአውሮፓ አህጉራዊ ዋንጫ ታሪክ በፍፃሜ የተሰለፈው የመጀመሪያው ግብ ጠባቂ ዚምባብዌያዊው ብሩስ ግሮብላር ሲሆን ይሄም በ1985 በአውሮፓ ዋንጫ ፍፃሜ የተጻፈ ታሪክ ነው።

ሜንዲ ባለፈው ውድድር ዘመን በሁሉም ውድድሮች 19 ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርበት በመጠበቁ የአውሮፓ የ2020-21 ምርጡ ግብ ጠባቂ ተብሎ ተሸልሟል።

ሜንዲ በፍራንስ ፉትቦል የሚዘጋጀው የባለንዶር ሽልማት የያሺን ሽልማትን ባያገኘም ከዕጩዎቹ መካከል አንዱ ነበር።

ታቲያና ስኩንማርከር

አገር፡ ደቡብ አፍሪካ

ዕድሜ፡ 24

የስፖርት መስክ፡ ውሃ ዋና

ታቲያና በቶኪዮ ኦሊምፒክ በውሃ ዋና የወርቅና የብር ሜዳሊያ ለአገሯ ደቡብ አፍሪካ ከማስገኘቷም በላይ በ200 እና 100 ሜትር የዓለምና የኦሊምፒክ ክብረ ወሰንን መስበር ችላለች።

ታቲያና በሪዮ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ባደረገችው ውድድር በሽራፊ ማይክሮሰከንድ ተሸንፋ በመውደቋ ከስፖርቱ ዓለም ራሷን ለማግለል ጫፍ ደርሳ ነበር።

ነገር ግን ተስፋ ባለመቁረጥ ወደፊት በመግፋት በርካታ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ድሎችን ተጎናፅፋለች።