ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ሠራዊት ጋሸናንና ሸዋ ሮቢትን ጨምሮ በርካታ ቦታዎችን ከአማጺያኑ በማስለቀቅ መቆጣጠሩ ተገለጸ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እየተመራ ያለው የኢትዮጵያ ጦር ጋሸናን ጨምሮ ሌሎች ቁልፍ ቦታዎችን መቆጣጠሩን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ዛሬ ኅዳር 22/2014 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ መከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል ኃይሎች በጋሸና ግንባር፤ አርቢት፣ አቀት፣ ዳቦ እና ጋሸና ከተሞችን ተቆጣጥረዋል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በበኩሉ በትዊተር ገጹ ላይ በሸዋ ግንባር ሸዋ ሮቢት ከተማን ጨምሮ፤ ሞላሌና መዘዞ ከተሞች ከህወሓት ነጻ ወጥተዋል ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም በወረኢሉ ግንባር የመንግሥት ጦር ጃማ ደጎሎ፣ ወረኢሉ፣ ገነቴ፣ ፊንጨፍቱ፣ አቀስታ ከተሞች ነጻ ሆነዋል ሲል ጽህፈት ቤቱ በትዊተር ገጹ አመልከቷል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚንስትሩ "ለቀጣይ ድሎች ማስፈንጠሪያ እና ለሕዝብ ሐሴት የሚፈጥር ነው" ባሉት መግለጫቸው የአገሪቱ ሠራዊት ጋሸናን መቆጣጠሩ፤ በላሊበላና በሰቆጣ፣ በወልዲያና በደሴ በህወሓት አማጺያን የተያዙ አካበቢዎችን "በአጭር ጊዜ ነጻ ለማውጣት መንገድ ከፋች ነው" ብለዋል።
በዚህ ግንባር በርካታ የነፍስ ወከፍና የቡድንና ከባድ የጦር መሣሪያዎች ከአማጺያኑ ኃይል መማረኩንም ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ጦሩም ወደ ላሊበላ፣ ወልዲያ እና ወገል ጤና አቅጣጫ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አክለዋል።
መንግሥት በቁጥጥሩ ስር መልሶ አስገባኋቸው ስላላቸው አካባቢዎች ከህወሓት በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።
መንግሥት የተለያዩ አካባቢዎችን መቆጣጠሩ የተነገረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የህወሓት አማጺያን ለመዋጋት ወደ ጦር ሜዳ ሄደው በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጦራቸው ጋሸናን እንደሚይዝ ከተናገሩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ማክሰኞ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ባስተላለፉት መልዕክት ከህወሓት ጎን የተሰለፉ ተዋጊዎች በሙሉ እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበው ነበር።
ከህወሓት ጋር ተሰልፈው የሚገኙ ተዋጊዎች ለኢትዮጵያ ሠራዊት እጃቸውን በመስጠት ራሳቸውን እንዲያተርፉ እና "የትግራይ ወላጆችም ልጆቻችን የት ደረሱ" ብለው እንዲጠይቁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል በወረኢሉ ግንባር የጃማ ደጎሎ፣ ወረኢሉ፣ ገነቴ፣ ፊንጨፍቱ እና አቀስታ ከተሞች ሙሉ በሙሉ ከህወሓት አማጺያን ነጻ መሆናቸውንና ጦሩ ወደፊት እያመራ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።
በሸዋ ግንባርም፣ የመዘዞ ፣ ሞላሌ ፣ ሸዋ ሮቢት እና አካበቢው እንዲሁም ራሳ እና አካባቢው ነጻ መውጣታቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል በምሥራቅ ግንባር (በአፋር) ካሳጊታ፣ ጭፍቱ፣ ዋኢማ፣ ጭፍራ፣ ድሬሮቃ፣ አለሌ፣ ሱሉላ ከተሞች ነጻ መውጣታቸውን ያስታወሱት ለገሰ (ዶ/ር) የአካባቢው አስተዳደር ወደ ቦታው ተመልሶ አካባቢውን መልሶ እያደራጀ መሆኑን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ ማስተዳድር ይልቃል ከፋለም (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ መንግሥት ላቀረበው ጥሪ ሕዝቡ ለሰጠው ምላሽ ምስጋና አቅርበው፤ አማጺው ቡድን "ራሱም ሆነ የዘረፈው ንብረት እንዳይወጣ ሕዝቡ እርምጃ ይውሰድ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ባለፈው ሰኔ ወር ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ እስካሁን እየተካሄደ ይገኛል።
የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልል በመግባት ዘመቻ በማካሄዳቸው በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የተለያዩ ቦታዎችን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ለማቅናት ፍላጎት እንዳለቸው እየገለጹ ቆይተዋል።
የደቡብ ወሎ ቁልፍ ከተሞች ደሴና ኮምቦልቻ በአማጺ መያዛቸውን ተከትሎ ጦርነቱ ወደ ሰሜን ሸዋ አካባቢ ተቃርቦ የነበረ ሲሆን፣ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ከባድ ውጊያዎች ሲካሄዱ መቆየታቸው ይነገራል።
ባለፈው ሳምንትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር በመሄድ ሠራዊቱን ለመምራት መወሰናቸውን ተከትሎም በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ለማስለቀቅ ውጊያዎች ተጠናክረው ሲካሄዱ ነበር።