በመቀለ ከተማ አርብ ዕለት የአየር ጥቃት መፈጸሙን ነዋሪዎች ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, AC
አርብ ኅዳር 17/2014 ዓ.ም በትግራይ ክልል መዲና መቀለ ከተማ የአየር ጥቃት መፈጸሙን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለጹ።
በጥቃቱ የሰው ሕይወት ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ የዓይን እማኞች ጨምረው ተናግረዋል።
ዳያስፖራ እና የሳምረ መንገድ በመባል በሚታወቁት አካባቢዎች ላይ የአየር ጥቃቱ እንደደረሰም አክለዋል።
ዛሬ ጠዋት 3 ሰዓት አካባቢ ዳያስፖራ በሚባለው ቦታ እና ከቀኑ 6 ሰዓት ተኩል ደግሞ የሳምረ መንገድ በተባለው አካባቢ ጥቃት እንደደረሰ የዓይን እማኞቹ ተናግረዋል።
በጥቃቱ ሳቢያ ቤታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪ አቶ ገዛኢ መድሕን ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ዳያስፖራ በሚባለው አካባቢ ሰላማዊ ሰው ብቻ ነው የሚኖረው። ወታደራዊ ወይም ሌላ ነገር በአካባቢው የለም። ሰላማዊ ሰዎች ተሰብስበን በነበርንበት ሰዓት ነው ጥቃት የተፈጸመው። እኔ እና ቤተሰቦቼ ታችኛው የቤቱ ክፍል ስለነበርን በእኛ ላይ የደረሰ ጉዳት የለም። ቤታችን እና ንብረታችን ግን ወድሟል። ለዓመታት ለፍተን ያፈራነው ቤትና ንብረት ነው የወደመብን። በጣም ተደናግጠናል" ብለዋል።
የአቶ ገዛኢ ባለቤት አራስ እንደሆነች እና በጥቃቱ በጣም እንደተደናገጠች ለቢቢሲ ገልጻለች።
"አራስ ነኝ። ሕጻን ልጅ ይዣለሁ። ልጆቼን ቁርስ እያበላሁ ነበር። ከዛ አውሮፕላን መጣች አሉ። ሸሽተን ተሰብስበን ሌላ ክፍል ገባን። ወታደር በሌለበት ሰላማዊ ሰፈር ላይ ነው ድብደባው የተፈጸመው። ይህ ጭካኔ የተሞላበት ነው" በማለት አስረድታለች።
ሌላ ቢቢሲ ያናገራቸው የእድሜ ባለጸጋ በጥቃቱ ቤታቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተናግረዋል።
"የወደመው ንብረት ነው እንጂ በሕይወት ተርፈናል" ብለዋል።
የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ የድሮን ጥቃቱ የተፈጸመው ሲቪል ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ ነው፤ ሲሉ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል። ከፌደራል መንግሥት በኩል እስካሁን ስለ ጥቃቱ በይፋ የተባለ ነገር የለም።
ማብራሪያ እንዲሰጡ ዛሬ ጠዋት የደወልንላቸው የመንግሥት ኮሙንኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ መረጃ እንደሌላቸው አሳውቀውናል።
ከሰዓት ተጨማሪ መረጃ ለመጠየቅ ብንደውልም አልተሳካልንም። የመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሌኔል ጌትነት አዳነን ለማግኘት ብንደውልም ምላሽ አላገኘንም።
አንድ ዓመት የሞላው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በጥቅምት ወር ተባብሶ ከቀጠለ በኋላ መንግሥት በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ላይ በሚገኙ ኢላማዎች ላይ የአየር ጥቃት ሲፈጽም መቆየቱ ይታወሳል።
ቀደም ሲል የአየር ድብደባዎች ሲፈጸሙ በኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት በኩል መግለጫ ሲሰጥ ነበር።












