በአዲስ አበባ በሁለት ኤምባሲ በሮች ላይ የተደረጉት ሰልፎች ምን መልዕክት ተላለፈባቸው?

የፎቶው ባለመብት, Gashaw Shibabaw
በትናንትናው ዕለት ሃሙስ ሕዳር 16 በአዲስ አበባ መቀመጫቸውን ባደረጉት የአሜሪካ እና እንግሊዝ ኤምባሲ ደጃፎች ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተቃውሞ መልክት አስተላልፈዋል።
ሰልፉን ያሰተባበሩት የሲቪል ማህበራት ጥምረት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰኘ ስብስብ ሲሆን የጥምረቱ ፕሬዚዳንት አቶ ጋሻው ሽባባው ዓላማውን ሲያስረዱ «ለኢትዮጵያ ፍትህን ለመጠየቅ ያደረግነው ሰልፍ ነው» ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጋሻው እንደሚሉት ሰልፉ ከመከናወኑ በፊትም ከቀኑ ሰባት ሰዓት በመላው አገሪቱ ያሉ መኪኖች ለ10 ደቂቃ ጥሩንባቸውን እያሰሙ እና መብራት እያበሩ የሚሄዱበት መርሃ-ግብር የትዕይንቱ አካል እንደነበር እና የተቃውሞ ሰልፉ በሁለት ተከፍሎ ተከናውኗል።
መኪኖቹ ጥሩምባቸውን ለመጀመሪያው አንድ ደቂቃ እንዲያሰሙ ቀጥሎም መብራታቸውን ደግሞ ለቀጣይ ዘጠኝ ደቂቃዎች እንዲያበሩ የታቀደ እንደነበርም አክለዋል።
ወደ ኤምባሲዎቹ የሄዱት ሰልፈኞች "በጠራራ ጸሃይ ፋኖስ ይዘው መሄዳቸው እንዲሁም መኪኖች በቀን መብራት ማብራታቸው የፍትህን ጥያቄ የሚያመላክት" እንደሆነም የጥምረቱ ፕሬዚዳንት ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Gashaw Shibabaw
"የእንግሊዝ አምባሳደር ደብዳቤውን ጠብቀው ተቀብለውናል ለዚህም ትልቅ ምስጋና አለን" ያሉት አቶ ጋሻው፤ "የአሜሪካ ኤምባሲ በታንክስ ጊቪንግ (አመታዊው የምስጋና በአል) በአል ምክንያት ስራ ባለመኖሩ ለጥበቃዎች ደብዳቤውን ሰጥተን ተመልሰናል" ብለዋል።
ደብዳቤዎቹ አገራቱ የፈረሟቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እንዲያከብሩ፤ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መግባታቸውን እንዲያቆሙ እና ፍትሐዊ እንዲሆኑ መጠየቃቸውን አቶ ጋሻው ያስረዳሉ።
"ጣልቃ ገብነት ተብለው በሰልፈኞቹ የተገለጹት ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት ዕድል ስምምነት (አጎዋ) እንድትወጣ መወሰኑ፣ ሲቪል ማህበራቱ ታዝበን ከምርጫ ቦርድ ጋር እውቅና የሰጠነውን መንግሥት ወደ ጎን የሚያደርግ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም መሞከር፣ በሕዳሴ ግድቡ ላይ ሲታዩ የነበሩ ጣልቃ ገብነቶች እንደሚገኝበትም" አቶ ጋሻው ገልጸዋል።
እስካሁን ድረስም ለሁለቱ ኤምባሲዎች የተላከውን ደብዳቤ ግልባጭም ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ለአውሮፓ ሕብረት አና ለተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እስከ ሰኞ ድረስ ለማስገባት እየሰሩ እንደሆነም ተናግረዋል።
ለሰልፉ መነሻነትም በውጪ አገራት እየተደረጉ ያሉ ሰልፎች መሆናቸውን የገለጹት ጋሻው "እስከአሁን ድረስ ይህ ሰልፍ በ18 የተለያዩ ግዛቶች ውስጥ የተደረገ ሲሆን በሁሉም 53ቱም ግዛቶች ውስጥ ይደረጋል ብለን ነው የምናነው። እንግሊዝ ውስጥም ሰልፉ ተደርጓል። ስለዚህ በውጪው አለም እንደዛ እየተደረገ አገር ውስጥ ያሉ ኤምባሲዎች ሄዶ ጥያቄ አለማቅረቡ ትክክለኛ ነው ብለን አናምንም" ብለዋል።
ሰልፉ የመንግሥት ተወካዮች እንዲሁም ማህበራዊ አንቂዎች ለመሳተፍ ቢጠይቁም ፈቃድ መከልከላቸውን እና ይህም ሰልፉን ከፖለቲካ ፓርቲ ጋር እንዳይያዝ በማሰብ ነው ብለዋል።
"ከሁለቱም አገራት ጋር ያለን ግንኙነት ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ነው። የአሜሪካም ሆነ የአንግሊዝ አባቶች እና አያቶች ጠብቀው ያቆዩት የሕዝቦች እና የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዳይበላሽ ነው የጠየቅነው" ሲሉ ጋሻው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ቢቢሲን ጨምሮ ሲኤንኤን፣ ሮይተርስ እና አልጀዚራ የሙያ ስነ-ምግባራቸውን እንዲጠብቁም ጠይቀናል። የመገናኛ ብዙሃን ሚና በተለይም በሌሎች አፍሪካ አገራት ላይ የነበረው ሚና ይታወቃል። ስለዚህም ለሁሉም ወገን ነገሮችን በእኩል አይን ማየት ይገባቸዋል" ሲሉም ተናግረዋል።
ይህንን የተመለከተ ደብዳቤ መጻፋቸውን እና ይህንንም እስከ ሰኞ ድረስ ለማድረስ ማቀዳቸውን ተናግረዋል።












