ሰዎችን በማሰቃየት የሚወነጀሉት የኢሚሬትሱ ጀነራል የኢንተርፖል ፕሬዝደንት ሆኑ

ሰዎችን በማሰቃየት የሚወነጀሉት የዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ (ዩኤኢ) ጄኔራል የዓለም አቀፉ ፖሊስ ኢንተርፖል ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ።

የኢንተርፖል ፕሬዝደንት ሆነው የተመረጡት አሕመድ ናሲር አል-ራይሲ የዩኤኢ አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢንስፔክተር ጀነራል ናቸው።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡደኖች ጀነራል እንዳይመረጡ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ቢቆዩም አልተሳካላቸውም።

ጀነራል ራይሲ ሰዎችን አሰቃይተዋል ተብሎ የሚቀርብባቸውን ክስ ያጣጥላሉ።

የዩናይትድ አረብ አሜሬትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "እኛ በፖሊስ የሚፈፀመው አላግባብ የሆነ ድርጊትን አንታገስም" ብሏል።

ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ኢንተርፖልን የሚያስተዳድሩት ራይሲ ከሶስት ዙር ምርጫ በኋላ ነው ኢስታንቡል ውስጥ በተደረገ ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዝደንት ሆነው የተመረጡት።

የኢንተርፖል ፕሬዝደንት ሆነው የሚመረጡ ሰዎች ደሞዝ አይከፈላቸውም፤ ይልቁንስ እንደ በጎ ፈቃደኛ ነው የሚያገለግሉት።

ጀነራሉ የኢንተርፖል ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴን መሰብሰብ ዋነኛ ሥራቸው ይሆናል። ኮሚቴው ደግሞ የዋና ፀሐፊው ጀነራል ዩርገን ስቶክን ተግባራት ይገመግማል።

ጀነራል ዩርገን ስቶክ ሙሉ በሙሉ ጊዜያቸውን ለኢንተርፖል ሰጥተው መሥሪያ ቤቱን የሚያስተዳድሩ ደመወዝተኛ ናቸው።

ጀነራል ትዊተር ገፃቸው ላይ በለጠፉት መልዕክት በመመረጣቸው "ክብር" እንደተሰማቸው ገልፀው ድርጅቱን የበለጠ ለማጠንከርና ለሁሉም ደኅንነት የሚሠራ ለማድረግ እንደሚጥሩ ገልጸዋል።

ዩኤኢ በዓለማችን ካሉ "እጅግ ሰላማዊ ሥፍራዎች አንዷ ናት" ያሉት አዲሱ ፕሬዝደንቱ፤ የባህረ ሰላጤው አገራት "በከባድ ቀጠና ውስጥ ቢኖሩም ለውጥ እያመጡ ያሉ ናቸው" ብለዋል።

ነገር ግን ሂዩማን ራይተስ ዎች የተሰኘው የመብት ተሟጋች ቡድን የገልፍ ባሕረ ሰላጤ አጥኚ የሆኑት ሂባ ዛያዲን "ለሰብዓዊ መብት አሳዛኝ ቀን ነው ዛሬ" ሲሉ የሰውዬውን መመረጥ ተቃውመዋል።

አጥኚዋ እንዳሉት "ጀነራሉ በቀጠናው ከሚገኙ ጠቅልለህ ግዛ አስተዳደሮች የአንዷ ተወካይ ናቸው፤ ሰላማዊ ተቃውሞን ሽብርተኝነት የምትል ሃገር ተወካይ ናቸው" ሲሉ ሞግተዋል።

ገልፍ ሴንተር ፎር ሂዩማን ራይትስ የተሰኘው ተቋም ጠበቃዎችም ኦፊሴላዊ የተቃውሞ ደብዳቤ ለፈረንሳይና ለቱርክ አስገብተዋል።

ጠበቃዎቹ ጀነራል ራይሲ የዩኤኢ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን በሕገ-ወጥ መንገድ አሥረው አሰቃይተዋቸዋል ሲሉ ይከሳሉ። ከእነዚህ መካከል ደግሞ በፈረንጆቹ 2017 በቁጥጥር ሥር ውሎ የሃገሪቱን ስም በማሕበራዊ ሚድያ አጥፍተሃል ተብሎ 10 ዓመት እሥር የተፈረደበት አሕመድ ማንሱር አንዱ ነው።

የዩኤኢ ፕሬዝደንት አማካሪ አንዋር ጋርጋሽ ጀኔራሉ ላይ እየቀረቡ ያሉ ወቀሳዎች የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል።