ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አይንስታይን የአንጻራዊነት ንድፈ ሐሳብን ያረቀቀባቸው ወረቀቶች በሚሊዮን ዶላሮች ተሸጡ
ታላቁ ሳይንቲስት አልበርት አይንስታይን የአንጻራዊነት ንድፈ ሐሳብን (Relativity Theory) ለማርቀቅ ቁጥሮችን የቀመረባቸው፣ ደምሮ የቀነሰባቸው ወረቀቶች ለጨረታ ቀርበው ከፍተኛ ዋጋን አወጡ።
ወረቀቶቹን ለጨረታ ያቀረበው ፓሪስ የሚገኘው ክሪስቲ የጨረታ ማዕከል ነው።
እነዚህ በርካታ ስሌቶችና ቁጥሮች የተሞነጫጨሩባቸው ወረቀቶች 11 ሚሊዮን ዶላር በሆነ ዋጋ ተሽጠዋል።
አንድ የሳይንሳዊ ወረቀት ሰነድ እንዲህ ባለ ዋጋ ሲሸጥ የአልበርት አይንስታይን በታሪክ የመጀመርያው ውዱ ሰነድ ሆኖ ተመዝግቧል።
የአንጻራዊነት ንድፈ ሐሳብ ተብሎ የሚጠራው የጥናት ወረቀት እንደ ጎርጎሮሲያኑ በ1915 ዓ.ም ነበር የታተመው።
ይህ ሳይንሳዊ ቀመር የሰው ልጆች የቦታ፣ የጊዜ እና የስበት ሕግን የሚረዱበትን መንገድ ከሥር መሠረቱ የቀየረ ነው።
ይህ ቀመሮች የተቸከቸኩበት የወረቀት ክምር ከ1913 እስከ 1914 በአይንስታይንና በስዊዛዊው ጓደኛው ሚሼል ቤሶ የተጻፈ ሲሆን፣ ቤሶ ሰነዶቹን ከእርሱ ዘንድ አቆይቷቸው ስለነበር ነው ለጨረታ መቅረብ የቻሉት።
የክሪስቲስ የጨረታ ድርጅት ስዊዛዊውን ሚሼል ቤሶን እነዚህን ወረቀቶች ለታሪክ እንዲበቁ ከእሱ ዘንድ በማቆየቱና በአርቆ አስተዋይነቱ ከፍ አድርጎ አሞካሽቶታል።
"ብዙውን ጊዜ አይንስታይን ወረቀቶችን የሚያስቀምጥ ሰው አልነበረም። ቀመሮችን ካሰላ በኋላ ከእሱ ጋር አያቆያቸውም። ይህ ሰነድ ለዚህን ያህል ዘመን መቆየቱ እጅጉኑ አስገራሚ ነገር ነው" ብለዋል በክሪስቲስ የጨረታ ማዕከል የሚሰሩ አንድ ባለሙያ።
እነዚህ የተቸከቸከባቸው ወረቀቶች አይንስታይን በጥቁር እስክሪብቶ ቁጥሮችን ያሰላባቸው ናቸው ተብሏል።
በድምሩ 54 ገጽ ወረቀቶች ሲሆኑ፣ ወረቀቶቹን በ11 ሚሊዮን ዶላር የገዛው ግለሰብ ማንነት እስከ አሁን አልታወቀም።
ይህ የአይንስታይን ቀመር በተለይ የሰው ልጅ የሁለንተና (universe)፣ የፕላኔቶች እሽክርክሪት እና የብላክ ሆልስ ምሥጢራት ዙርያ አዲስ ግንዛቤን ያስጨበጠ ነው።
ባለፈው ግንቦት በተመሳሳይ የአይንስታይን ዝነኛ ቀመርን የሆነችውን (E=mc²) የያዘች አንዲት ደብዳቤ በአንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ ዶላር መሸጧ አይዘነጋም።