ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስድስት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ከእስር ተለቀቁ
ኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች መካከል ስድስቱ መፈታታቸውና ሌሎች አምስት በእስር ላይ እንደሚገኙ ድርጅቱ ገለጸ።
የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ እንዳሉት በእስር ላይ ካሉት የድርጅቱ ሠራተኞች ጋር አንድ የቤተሰብ አባልም በቁጥጥር ስር እንዳለ አስታውቀዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ 16 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች የታሰሩ ሲሆን አሁን የተፈቱት ከእነዚህ መካከል ናቸው።
ከሰሞኑ በእስር ላይ ከነበሩ ከሰባ በላይ የድርጅቱ የእርዳታ መኪና አሽከርካሪዎች መካከል ግማሾቹ መለቀቃቸው ተገልጿል።
ታስረው ከነበሩት የድርጅቱ ኮንትራት ሠራተኞች መካከል 34ቱ አሽከርካሪዎች ቢፈቱም ሌሎች 36 በእስር ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም 72 የከባድ መኪና አሸከርካሪዎች አፋር ክልል ሰመራ ውስጥ ባለፈው ሳምንት አርብ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘግቦ ነበር።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስሩን በተመለከተ እንዳለው "የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች በቁጥጥር ስር የመዋል ሪፖርቶች ከሚሰሩበት ድርጅት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም" ብሏል።
ጨምሮም "ፖሊስ ለታሰሩበት ምክንያት ማስረጃ ካላገኘ እነዚህ ግለሰቦች ከእስር ይለቀቃሉ" ሲልም ገልጿል።
ኢትዮጵያ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጇን ተከትሎ በአገሪቱ በርካታ ሰዎች መታሰራቸው ሪፖርት እየተደረገ ነው።
እስሩ የተወሰነ ማኅበረሰብ ላይ አነጣጥሯል ቢባልም ባለሥልጣናቱ በበኩላቸው የትኛውንም ማኅበረሰብ ኢላማ እንላደረገና በቁጥጥር ስር የዋሉት የአስቸኳይ ጊዜ ሕጎችን የጣሱ ናቸው ብለዋል።
ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረውና በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንደቀጠለ ሲሆን የፌደራል መንግሥት ኃይሎች ከአማፂያን ጋር እየተፋለሙ ይገኛሉ።
በጦርነቱ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ሰዎች ሲገደሉ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል፣ በመቶ ሺዎች በረሃብ አፋፍ ላይ ሲሆኑ ካለው የአገሪቷ ሰብዓዊ ቀውስ ጋር ተያይዞም መንግሥትና አማፂያኑ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ዓለም አቀፍ ጥሪዎች እየቀረቡ ይገኛሉ።
ተፋላሚ ወገኖች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በረሃብ ላይ የሚገኙ ሚሊዮኖችን ህይወት የማዳን እርዳታ እንዲመቻችና ሰብዓዊ አገልግሎቶች እንዲደርሱ አገራትና ተቋማት ጫና እያደረጉ ይገኛሉ።