ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኦሮሚያ ክልል የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በአገሪቱ ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ ሕገወጥ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር በመላው ክልሉ ውስጥ የሰዓት እላፊ ገደብ ጣለ።
የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ግዛቸው ገቢሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የሰዎችና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴን በመለየት ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋቱ 11፡30 ድረስ እንቅስቃሴ ማድረግ ተከልክሏል ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ሰዎች መንቀሳቀስ የሚችሉት ከንጋቱ 11፡30 እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ሲሆን ተሸከርካሪዎች ግን መንቀሳቀስ የሚችሉት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ብቻ መሆኑን አቶ ግዛቸው ተናግረዋል።
ጨምረውም ከሰዓት እላፊው በተጨማሪ "በመንገድ ላይ ፍተሻዎች ይኖራሉ። ድንገተኛ ፍተሻ ይካሄዳል፤ በኬላዎችም ላይ ፍተሻ ይደረጋል። በመንግሥት መስሪያ ቤቶችና ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎችም ፍተሻዎች ይካሄዳሉ" ብለዋል።
አቶ ግዛቸው ገቢሳ አብዛኛዎቹ ፍተሻዎች ምሽት ላይ የሚካሄዱ መሆናቸውን ጠቁመው ፍተሻዎቹ ዘላቂ ላይሆን ይችላሉ ብለዋል።
በትግራይ የተቀስቀሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወደ አጎራባች አማራ እና አፋር ክልል ተስፋፍቶ የህወሓት አማጺያን የደቡብ ወሎ ከተሞችን ከያዙ በኋላ የፌደራሉ መንግሥት በመላ አገሪቷ ተፈጻሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል።
የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጨምረው ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የሚገኙ አከራዮች የተከራዮቻቸውን መታወቂያ በመያዝ በቀበሌና በአቅራቢያቸው በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች እየሄዱ ማስመዝገብ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
"አዲስ ተከራይ፤ ያለመታወቂያ ቤት ማከራየት የለባቸውም። መታወቂያ የሌላቸው ተከራዮች ካሉም መታወቂያ እንዲያወጡ ጊዜያዊ አሰራር ተዘርግቷል" ሲሉ አቶ ግዛቸው ተናግረዋል።
ምክትል ኃላፊው በክልሉ ይህን መሰል አዋጅ ማውጣት ያስፈለገው "ሰርጎ ገቦች በክልል ሰላም እንዳያደፈርሱ ለመከላከል ነው" ብለዋል።
"በአገር አቀፍ ደረጃ የተረጋጋ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቀሴዎችን የሚያደርጉ አካላት ሰርገው ገብተው ሕዝብ እና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ በሚል ነው" ሲሉ ክልሉ ውስጥ የተጣለውን የሰዓት እላፊ ገደብ ምክንያት አብራርተዋል።
በክልሉ የተለየ ስጋት የለም የሚሉት አቶ ግዛቸው፤ "ነገር ግን እንደ አገር ያሉ የፀጥታ ችግሮች ይታወቃሉ። ከዚህም በተጨማሪ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች የህብረተሰቡን የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያናጉ ሕገ-ወጥ የመሳሪያ ዝውውርና ሕገ-ወጥ የንግድ ተግባራት አሉ። እነዚህን ለመከላከል ታስቦ ነው የሰዓት እላፊው የተጣለው" ብለዋል።
ይህን የመንግሥት አዋጅ ተከትሎ የዜጎች መብት እንዳይጣስ በመንግሥት የጸጥታ አስከባሪ አካላት ከፍተኛ ጥንቃቄ ይካሄዳል ያሉት አቶ ግዛቸው፤ የአዋጁ መመሪያ ለጸጥታ አስከባሪ አካላት ተላልፏል ይላሉ።
የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዱኛ አሕመድ ሕገወጥ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉንና ከዚሁ ጋር በተያያዘም በክልሉ ውስጥ መሳሪያ ያላቸው ነዋሪዎች በአስር ቀናት ውስጥ እንዲያስመዘግቡ መታዘዙን ለፋና ተናግረዋል።
ከህወሓት ጋር አጋርነት የፈጠረውና በሽብርተኝነት የተፈረጀው መንግሥት ሸኔ የሚለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ ጥቃት ሲፈጽም መቆየቱ ይታወሳል።