በፋኖ አደረጃጀት ያለ ማንኛውም የታጠቀ ኃይል በመንግሥት መዋቅር ስር እንዲገባ ተጠየቀ

በፋኖ አደረጃጀት ለሰለጠኑና ወደ ጦር ግንባር የመዝመት ፍላጎት ላላቸው ማንኛውም የታጠቀ ኃይል በመንግሥት መዋቅር ውስጥ እንዲገቡ ተጠየቀ።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት ኮማንድ ፖስት ሰኞ ዕለት ጥቅምት 29/2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በአደረጃጀቱ ስር ለሰለጠኑና ለሚዘምቱ አስተዳደሩ ማንኛውም የሎጅስቲክ ድጋፍ የሚያቀርብ መሆኑን አስታውቋል።

መግለጫው በፀጥታ ምክር ቤቱ ወይም በሰላምና ደኅንነት ቢሮ ስምሪት ሳይቀበል መሳሪያ ታጥቆ በከተማዋ በተለያዩ ስፍራዎች የጦር መሳሪያ ይዞ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ተጠያቂ እንደሚሆንም አሳስቧል።

ኮማንድ ፖስቱ በተጨማሪ በባሕር ዳር ከተማ ያልተመዘገበ ማንኛውም የግል የጦር መሳሪያ በየአካባቢው በሚገኙ ሚሊሻ ጽህፈት ቤት እንዲያስመዘግቡም ጠይቋል።

የከተማዋ የፀጥታ ምክር ቤት እንዳለው የሚመለከታቸው ሰዎች ከጥቅምት 29 እስከ ኅዳር 5/2014 ዓ.ም ባሉት አምስት ቀናት ተመዝግበው እንዲያጠናቅቁ አሳስቧል።

አራት ነጥቦችን ባካተተው የኮማንድ ፖስቱ መግለጫ፣ በጦሩ ግንባሩ በነበረ ዘመቻ ላይ ማንኛውንም የጦር መሳሪያና ትጥቅ ይዘው ወደ ባሕር ዳር ከተማ ለተመለሱም ግንባር የመሄድ ፍላጎት ያላቸው መንግሥት ባወጣው አደረጃጀት ታቅፈው ወደ ግንባር እንዲሄዱም አሳስቧል።

ሆኖም ከመንግሥት የፀጥታ ኃይል ውጪ መሳሪያ ይዞ በከተማዋ በተለያዩ ስፍራዎች ሲንቀሳቀስ የተገኘ ማንኛውም አካል በፀጥታ ኃይሉ ተጠያቂ እንደሚሆንም አስፍሯል።

ከተለያዩ የጦርነት ቀጠናዎች ተፈናቅለው ወደ ባሕር ዳር ለመጡ ተፈናቃዮችም በተዘጋጀው መጠለያ ካምፕ መግባት አለባቸው ተብሏል።

ወደ መጠለያ ካምፕ ለማይገቡት ደግሞ ማንኛውም አከራይ የተከራይ ግለሰቦችን መታወቂያ ኮፒ በማድረግ በአካባቢው ለሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ማሳወቅ አለባቸው ተብሏል።

ለዚህም የኮማንድ ፖስቱ የሰጠው ምክንያት "በተፈናቃይ ስም ሰርጎ ገቦች" እንዳሉ ስለተደረሰበት እና ለከተማዋም ደኅንነት በሚል ነው በማለትም ገልጿል።

የኮማንድ ፖስቱ ያወጣቸው እነዚህ ሃሳቦች መግለጫው ከወጣበት ጥቅምት 29/2014 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አምስት ቀናት ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው አሳስቦ ይህንን በማይፈፅሙ ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ማስጠንቀቂያ ተላልፏል።