ታላቁ ሩጫ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ተራዘመ

ህዳር 5/ 2014 ለ21ኛ ጊዜ ሊካሄድ የነበረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከቀናት በፊት በታወጀው የአስቸኳያ ጊዜ አዋጅ ምክንያት መራዘሙን የውድድሩ አዘጋጅ አስታውቋል።

'ቶታልኢንርጂስ' የሚል ስያሜ የተሰጠው የ2014 ታላቁ ሩጫ መቼ እንደሚካሄድ አዘጋጁ ወደፊት እንደሚያሳውቅም በድህረ ገጹ ትናንት ማምሻውን አስታውቋል።

ከ10 ቀናት በኋላ እንዲካሄድ ታቅዶ በነበረው ውድድር 25ሺ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቅ ነበር።

ባለፈው ዓመት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከተለመደው ጊዜ ውጪ ጥር ላይ በተከናወነው ታላቁ ሩጫ 12 ሺህ 500 ተሳትፈው ነበር።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላለፉት 20 ዓመታት ሲካሄድ የቆየ እና በርካታ ህዝብ የሚሳተፍበት የስፖርት ፌስቲቫል ነው።

በዓለም የአትሌቲክስ ውድድር የገዘፈ ስም ባለው አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ 1994 የተመሰረተው ታላቁ ሩጫ፤ እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ በድምሩ ወደ 600 ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎችን አስተናግዷል።

የመጀመሪያው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከ10 ሺህ ያነሱ ተሳታፊዎች የነበሩት ሲሆን ባለፉት ዓመታት ውድድሩ ከ40 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን አስተናግዶ ነበር።

በአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ ሩጫ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ውድድር፤ ከኢትዮጵያውን ባሻገር ከተለያዩ ዓለም ክፍሎች የሚመጡ የውጪ አገራት ዜጎችም የሚሳተፉበት ሆኗል።

ታላቁ ሩጫ ለጤና ከሚደረገውና አስር ሺዎች ከሚሳተፉበት ሩጫ በተጨማሪም፣ ለአሸናፊዎች የገንዘብ ሽልማት የሚያበርክትበት መደበኛ የውድድር ዘርፍም አለው።

የዘንድሮ ታላቁ ሩጫ ሊካሄድ 11 ቀናት ሲቀሩት መራዘሙ የተገለጸው ባለፈው ማክሰኞ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ትናንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በስሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሚቀጥሉት 6 ወራት ተፈጻሚ የሚሆን ነው።