ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኬንያ ፖሊስ ከኢትዮጵያ አዋሳኝ ድንበር ጋር በተያያዘ ማስተባበያ ሰጠ
በአገሪቱ ያለውን ጦርነት ተከትሎ የኬንያና ኢትዮጵያ ድንበር መዘጋቱን የኬንያ ሚዲያዎች ቢዘግቡም የአገሪቱ ፖሊስ ግን ድንበሩ እንዳልተዘጋ ገለጸ።
በተለይ ሲቲዝን የተባለው የአገሪቱ ቴሌቪዥን የኬንያ መንግሥት ላልተወሰነ ጊዜ ከኢትዮያ ጋር አዋሳኝ ድንበሮችን ለመዝጋት መወሰኑን ዘግቦ ነበር።
ነገር ግን ይህንን ተከትሎ የኬንያ ብሔራዊ የፖሊስ አገለግሎት ዘገባውን አስተባብሏል።
የፖሊስ አገለግሎቱ ባወጣው አጭር መግለጫ ላይ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ድንበር እንደተባለው አለመዘጋቱን አመልክቶ፣ ሆኖም ግን በአጎራባች አገራት ውስጥ ባለው የደኅንነት ሁኔታ ምክንያት በድንበር አካባቢ ፍተሻና ክትትሎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቋል።
መግለጫ በድፍኑ "በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ባሉ አሳሳቢ የደኅንነት ሁኔታዎች" ምክንያት የኬንያ የድንበር ቁጥጥር እንደጠበቀ ይግለጽ እንጂ ኢትዮጵያን በተናጥል በስም አልጠቀሰም።
ይሁንና ሲቲዝን ቴሌቪዥን ትናንት የብሔራዊ ፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑትን ብሩኖ ኢሾይ ሺዎሶን ጠቅሶ እንደዘገበው ኬንያዊያን በኢትዮጵያ እየተባባሰ ባለው ሁኔታ አካባቢያቸውን በንቃት እንዲከታተሉ ማሰሰባቸውን ዘግቧል።
የብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት ቢሮው መግለጫ ኬንያዊያን ሰነድ አልባ ስደተኞች ሲያጋጥሟቸው ለፖሊስ እንዲጠቁሙም ያሳስባል።
ኢትዮጵያና ኬንያ 800 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ድንበርን ይጋራሉ። ሁለቱ አገራት በተለይ በድንበር ተሻጋሪ የመሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጠናከረ ትብብር ማድረግ ጀምረዋል።
ከነዚህ የመሠረተ ልማት ትብብሮች ውስጥ ከሞምባሳ-ናይሮቢ- አዲስ አበባ የሚያገናኘው ግዙፍ አውራ ጎዳና ይጠቀሳል።
ከዚህም ባሻገር ላፕሴት የተባለው ኬንያን ጨምሮ ኢትዮጵያንና ደቡብ ሱዳንን በንግድ ያስተሳስራቸዋል የሚባለው የላሙ ወደብ ሁለቱን አገራት ይበልጥ ያስተሳስራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ኬንያ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮያዊያን ስደተኞች ወደ አገሯ ሊገቡ እንደሚችሉ ስጋት እንዳላት ስትገልጽ ቆይታለች።